የመስቀል በዓል በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

7

ደባርቅ: መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓሉ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ምዕመናን በተገኙበት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ተከብሯል።

 

የሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሰላም አባት ብጹዕ አቡነ እስጢፋኖስ የመስቀል በዓል የመስቀሉን መገኘት እያሰብን በደስታ የምናከብረው የፍቅር በዓል ነው ብለዋል።

 

መስቀል ንግሥት ኢሌኒ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልን ለማግኘት ከልብ በመሻት እና በመጸለይ ቅዱስ ተጋድሎ ያደረገችበት በመኾኑ የእናቶቻችንን ገድል የምንዘክርበት በዓል ነው ብለዋል።

 

መስቀል ድኅነት የተከናወነበት፣ የጥል ግድግዳ ፈርሶ በምትኩ ሰላም እና ፍቅር የታወጀበት ቅዱስ በዓል ነው ብለዋል።

 

ብጹዕነታቸው አክለውም ይሄን ታላቅ በዓል በሰላም እና በፍቅር፣ በመተሳሰብ ማክበር እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

በበዓሉ የተገኙት የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሳ መስቀል የጥል ግድግዳ የፈረሰበት የሰላም ምልክት ነው ብለዋል።

 

የመስቀል በዓልን ስናከብር በአብሮነት እና በመተሳሰብ ለሀገር ሰላም በመትጋት ሊኾን እንደሚገባም መክረዋል።

 

የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጌትነት ጸጋዬ የመስቀል በዓል ከአባቶች ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳው የጎላ በዓል ነው ብለዋል።

 

መስቀል የጥል ግድግዳ የፈረሰበት የአብሮነት በዓል በመኾኑ ከበዓሉ ዓላማ በመነሳት ለዘላቂ ሰላም እና ልማት በመትጋት መጭውን ጊዜ የተሻለ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

 

የበዓሉ ተሳታፊ ምዕመናንም በበኩላቸው በዓሉ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች በድምቀት መከበሩን ገልጸዋል።

 

የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ ዳራው በተጨማሪ ማኅበራዊ መስተጋብርን በማጎልበት በኩል ሚናው ጉልህ መኾኑን አብራርተዋል።

 

በቀጣይም የመተሳሰብ እና የአብሮነት ባሕልን በማጎልበት ማስቀጠል እንደሚገባ ተመላክቷል።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በመስቀል በዓል መታደም ልዩ ሀሴት ያጎናጽፋል” የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች
Next articleየመስቀል በዓል ጥልን በመስቀሉ አሸንፎ ተለያይተው የነበሩትን አንድ ያደረገ ነው።