
ጎንደር : መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል በዓል በጎንደር ከተማ ተከብሯል።በበዓሉ ከታደሙ የሃይማኖቱ ተከታዮች በተጨማሪ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎችም ተገኝተዋል።
ከእንግሊዝ ሀገር እንደመጣች የተናገረችው ካትሪን ጀምስ ወደ አፍሪካ ስትመጣ የመጀመሪያዋ መኾኑን ገልጻለች። ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱዋ በፊት በካሜሮን እና በግብጽ ቆይታ ማድረጓን ተናግራለች። በኢትዮጵያ ያማረ ጊዜ እያሳለፈች መኾኗንም ገልጻለች ።
ካትሪን የጎንደር የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓት የተለየ ድባብ አለው ብላለች። በበዓሉ ላይ የሚሳተፉ ካህናትና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች፣ በባሕላዊ ጭፈራ በዓሉን የሚያደምቁ ወጣቶች የበዓሉ ልዩ ድምቀት በመኾናቸው” ይህን በማየቴ ደስተኛ ነኝ” ብላለች።
ሌላኛው ከጀርመን እንደመጣ የተናገረው ሀንስ ጀፈርሰን ለሦስተኛ ጊዜ በዓሉን መታደሙን ተናግሯል። የመስቀል በዓል ልዩ ትዝታ በጎንደር ምን እንደሚመስል ለሌሎች ጓደኞቹ ለማሳየት ማሳታወሻ የሚሆኑ ምስሎችን በካሜራው ማስቀረቱን ገልጿል።
በመስቀል በዓል መታደም ልዩ ሀሴት ያጎናጽፋል ነው ያሉት ጎብኝዎቹ። በጎንደር ከተማ ያሉ የመስሕብ ቦታዎችን ለማየት እቅድ እንዳላቸው የተናገሩት ጎብኞቹ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ሌሎች ጎብኞች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ኃይሉ ማሞ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!