የመስቀል በዓል ሲከበር ጥላቻን እና መለያየትን በማስወገድ ሊኾን እንደሚገባ የጎንደር ከተማ ከንቲባ አሳሰቡ። 

5

ጎንደር: መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል በዓል በጎንደር ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እየተከበረ ይገኛል።

 

በበዓል አከባበሩ ላይ የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ፣ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘውን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች፣ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ሥርዓቱን ጠብቀው እያከበሩ ይገኛሉ።

 

በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው መስቀል በጨለማ ውስጥ ብርሃንን የምናይበት፤ መስቀል ከስጋ አልፎ ለነፍስ መድኃኒት ነው ብለዋል።

 

የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ከሃይማኖት ዳራው አልፎ ማኅበራዊ እሴት መገለጫ መኾኑን አንስተዋል።

 

መስቀል የመሰባሰቢያ የአንድነት በዓል መኾኑንም ገልጸዋል። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሰቀል የመስቀሉን ታሪክ መቀየሩንም ተናግረዋል።

 

መስቀሉ ሙታንን ሲያስነሳ፣ ለምጻምን ሲያነጻ በማየታቸው በምቀኝነት መቅበራቸውን አብራርተዋል።

መስቀሉ ከተቀበረበት ከ300 ዓመታት በኋላ በንግስት ኢሌኒ መገኘቱን አስታውሰዋል።

 

ከንግሥት ኢሌኒ መልካም ትምህርትን በመማር ስለ ወንድማማችነት እና አብሮነት በጽናት ልንፈላለግ ይገባል ነው ያሉት።

 

መስቀሉ በቆሻሻ ተቀብሮ መቆየቱን አስታውሰው ጥላቻ መለያየት እና መፈናቀል የዚህ ዘመን ቆሻሻ በመኾናቸው ልናስወግድ ይገባል ነው ያሉት።

 

ከአባቶች በመማር ፍቅርን እና አንድነትን ማስቀደም እንደሚገባም አሳስበዋል።

 

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መልካም ተግባር በመፈጸም ለትውልድ የሚበጅ ተግባር ማከናወን ይገባል” መጋቤ ሐዲስ መምህር ዜናዊ አሸተ
Next article“በመስቀል በዓል መታደም ልዩ ሀሴት ያጎናጽፋል” የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች