
ሁመራ፡ መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የመስቀል በዓል በሁመራ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
በዓሉ በተከበረበት መስቀል አደባባይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ መምህር ዜናዊ አሸተ፣ የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፣ የከተማው ከንቲባ እንኳየነህ ሙሉ፣ የየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ካህናትና ሊቃውንት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች እና የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።
ትምህርተ ወንጌል ያስተላለፉት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ መምህር ዜናዊ አሸተ ስለ ነገረ መስቀሉ ሲያስተምሩ “በክርስቲያኖቾ የዘወትር እንቅስቃሴ መካከል ሁሌ መስቀል አለ” ብለዋል።
በአንድ ወቅት ከሰዎች ክፋት የተነሳ መስቀሉ ተቀብሮ እንደነበር አስታውሰው ነገር ግን መስቀል በክርስቲያኖች ልብ እና ህሊና ለዘለዓለም የሚኖር መኾኑን አንስተዋል። በዚህ ዘመንም ዘመኑን የሚዋጅ መልካም ተግባር በመፈጸም ለትውልድ የሚበጅ ተግባር ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል።
“የመስቀል በዓልን በነጻነት ማክበር ከጀመርን ዛሬ አምስተኛ ዓመታችን ነው” ያሉት ደግሞ የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪና የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ናቸው። “አባቶች ይቅር እንድትባሉ ይቅር በሉ ብለው ያስተምራሉ። እኛም የበደሉንን ሁሉ ይቅር እንላለን። ነገር ግን እኛ ይቅር ስንል ይቅር የማይሉን አካላት አሉ” ብለዋል።
ጥቅም እና ገንዘብ ኀላፊ ነው፤ ሀገር እና ትውልድ ግን ቀጣይ ነው ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ለሀገር እና ለትውልድ ሲባል በእምነት በመጽናትና ወንድምን ለጥቅም አሳልፎ ባለመስጠት የአካባቢውን ሰላም በጋራ ማጽናት እንደሚገባ አመላክተዋል። ጦርነት አውዳሚ መኾኑን በመረዳት በአንድነት እና በፍቅር ለሰላም ልንቆም ይገባል ነው ያሉት።
የመስቀል በዓል በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ በዓል ከመኾኑ በተጨማሪ በዩኒስኮ የተመዘገበ የማይዳሰስ ቅርስ ነው ያሉት ደግሞ የሁመራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ እንኳየነህ ሙሉ ናቸው። መስቀል ክርስቶስ የተሰቀለበት እና ለሰው ልጆች የነጻነት ጮራ ያወጣበት መኾኑንም አቶ እንኳየነህ አንስተዋል።
ከንቲባው አክለውም መስቀል ሰማይና ምድር የታረቁበት የበረከታችን ምንጭ ነው። በመስቀል ላይ የክርስቶስ ደም ፈስሷል። በዚህም በዓለም ሁሉ ሰላም ታውጇል ብለዋል። የጠብ ግድግዳም የፈረሰበት መኾኑንም አንስተዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብም በላቡ እና በደሙ ያገኘውን ነጻነት በማጽናት ለዘላቂ ሰላም በጋራ መቆም እንዳለበት ጠቁመዋል።
መስቀሉ የአንድነት፣ የሰላም እና የፍቅር መገለጫ ነው ሲሉ የሃይማኖቱ ተከታዮችና አገልጋዮች ለአሚኮ ተናግረዋል። መስቀል ለክርስቲያኖች የድል መንሻ ዓርማ መኾኑን ጠቁመው እኛም በመስቀሉ ሰላምን እንሰብካለን ብለዋል። ቅድስት ኢሌኒ የተቀበረ መስቀሉን ቆፍራ እንዳወጣችው ሁሉ ክርስቲያኖችም በልባችን የተቀበረውን ፍቅር በመፈለግ በአንድነት መቆም አለብን ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!