
ደብረ ማርቆስ: መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በበዓሉ የሃይማኖት አባቶች የከተማዋ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የሃይማኖቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ ከተማ አሥተዳደር የመስቀል ደመራ በዓል በሰባቱ ዋርካ መስቀል ዓደባባይ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የየአብያተ ክርስቲያናት ካህናት፣ ዲያቆናት፣ መዘምራን እና ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የሞጣ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ፀሐይ ወንድም ባስተላለፉት መልዕክት ለመስቀሉ ክብር ስንሰጥ፣ የደመራውን በዓል ስናከብር፣ በመስቀሉ የተደረገው እርቅና እና የተገኘው ሰላም በሁላችን ልብ መገኘት ይኖርበታል ብለዋል። መስቀል የትዕግሥት፣ የእርቅ እና የሰላም ምልክት መኾኑን ዘወትር ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ሁሉም የከተማችን ነዋሪዎች ዛሬም እንደትናንቱ በከተማችን የሚከናወኑ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር እንቅስቃሴዎችን እውን ለማድረግ ሰላም እና ፀጥታ ማረጋገጥ ወሳኝ በመኾኑ ከጥምር ጦራችን ጎን በመሰለፍ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የሞጣ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አሥተዳዳሪ መልአከ ገነት መላኩ አስማረ የመስቀል ደመራ በዓል አንድነት እና መተሳሰብ በሚጎለብቱበት፣ ሃይማኖታዊ እና የባሕል እሴቶች በድምቀት የሚፀባረቁበት ሲኾን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ማክበር እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከብዙ ፍለጋ እና ድካም በኋላ የተገኘው ቅዱስ መስቀል ከሐጥያት ጥላ፣ ከጥፋት ጨለማ የወጣንበት ከሞት ወደ ሕይዎት የተሸጋገርንበት የነፍሳችን ብርሃን፣ የሕይዎታችን መብራት ነው ያሉት መልአከ ገነት መላኩ አስማረ የመስቀሉን ታሪክ አብነት አድርገን የቀደመ ሰላማችንን እና አንድነታችንን ለመመለስ በጋራ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
የሃይማኖቱ ተከታዮች በበኩላቸው የመስቀልን በዓል ስናከብር አሁን ካለንበት ሁለንተናዊ ችግር ለመውጣት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!