“መስቀሉ የሰላም ምልክት እና የፍቅር አርማ ነው” ብጹዕ አቡነ ሰላማ

2
ገንደውኀ፡ መስከረም 17 /2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል በዓል በምዕራም ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
የምዕራብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሴኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ሰላማ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላምን ፣ፍቅርን እና ድኅነትን ሰብኮበታል ብለዋል። ስለዚህ እኛም በዓሉን ስናከብር በመስቀሉ የተሰጠነንን ፍቅር ፣ሰላም እና ድኅነት በማስታወስ እና በማሰብ መኾን አለበት ነው ያሉት። የመስቀል በዓል አብሮነትን በማሳደግ ፣መከባበርን በማጉላት እና ለመስቀሉ ያለነን ፍቅር የሚያሳይ ነው ብለዋል።
“መስቀሉ የሰላም ምልክት እና የፍቅር አርማ ነው” ያሉት ብጹዑነታቸው ለሰላም መስፈን ሁሉም ማኅበረሰብ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል። በዓሉ ሲከበር የክርስቶስ መከራ እየታሰበ ሀገር ሰላም እንድትኾን በመጸለይ፣ በመተጋገዝ እና በመጠያየቅ ሊኾን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የምዕራብ ጎንደር ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አስያ ኡመር የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ መኾኑን ገልጸዋል።
በዩኔስኮ ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ መኾኑንም አንስተዋል። በዓሉ ሃይማኖታዊ ይዘቱን እና ትውፊቱን ጠብቆ መከበሩንም ገልጸዋል። የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ጠብቆ እና ተንከባክቦ ለትውልድ ለማስተላለፍ እና የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል። በዩኔስኮ ያልተመዘገቡ ቅርሶችን በማስመዝገብ የቱሪዝም ዘርፉን ማነቃቃት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ባሕልን ሳይበርዙ መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሐመድ የአካባቢያችን ሰላም በመጠበቅ ልማትን ማፋጠን አለብን ብለዋል። የትውልድ ክፍተት እንዳይፈጠር ትምህርት ላይ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልክም ጥሪ አቅርበዋል። የበዓሉ ታዳሚዎች የመስቀል በዓል ክርስቶስ ለሰው ልጆች የከፈለው ዋጋ የሚታሰብበት ነው ብለዋል።
በዓሉን በመረዳዳት፣ ለሌለው በማካፈል እና በመጠያየቅ እንደሚያከብሩትም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“በመስቀል ማዕበል ያልፋል፤ በመስቀል መከራ ይታለፋል”
Next articleየመስቀል ደመራ በዓል በሞጣ ከተማ እየተከበረ ነው።