
ባሕር ዳር: መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል በዓል በሀገራችን በሁሉም አካባቢዎች በየዓመቱ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡ በዓሉ ማኅበረሰቡ በጋራ ተሰባስቦ በዓደባባይ እና በየሰፈሩ የሚያከብሩት ሲኾን ለበዓሉ ማድመቂያ እንደየ አካባቢው ባሕል የተለያዩ ባሕላዊ ምግብ እና መጠጦች ይዘጋጃሉ፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የመስቀል በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ አብዚ የሚባለው ምግብ ከጤፍ የሚዘጋጅ እንጀራን በማነባበር እና የተለያዩ ማባያዎችን በመቀባት የሚዘጋጅ ባሕላዊ ምግብ ነው። በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ለክብረ በዓል፣ ለድግስ እና ለተለያዩ ማኅበረሰባዊ ኹነቶች የሚዘጋጅ ባሕላዊ ምግብ ነው አብዚ፡፡ በተለይም ይህ ምግብ የመስቀል በዓል በጋራ በሚከበርበት ጊዜ እንደሚቀርብ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡አብዚ የጤፍ እንጀራን በግብዓትነት በመጠቀም የሚዘጋጅ ምግብ ነው ያሉን በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንጅባራ ከተማ ነዋሪ እና የብሔረሰቡ ተወላጅ የኾኑት ወይዘሮ ሊሻንወርቅ መኮንን ናቸው፡፡ አብዚ እንጀራውን በትኩስ በማነባበር ወይም በመደራረብ የተለያዩ ማባያዎችን በመቀባት ይዘጋጃል ነው ያሉት፡፡
አብዚ ብዙ ዓይነት ሲኾን በፍስክ ጊዜ የአይብ አብዚ እና የቅቤ አብዚ (ቅቤ በአዋዜ) ይዘጋጃል፡፡ የአይብ አብዚ አይቡን በተለያዩ ቅመሞች በመቀመም የሚዘጋጅ ሲኾን የቅቤ አብዚ ደግሞ በርበሬን የተለያዩ ቅመሞችን በመጠቀም ከለጋ ቅቤ ጋር በማዋሃድ የሚዘጋጅ ነው ብለዋል፡፡ በጾም ጊዜም በሽሮ፣ በክክ ወጥ፣ በአዋዜ እና በኑግ ተቀብቶ እንደሚዘጋጅ ነው የነገሩን፡፡አብዚ በተለይም ለመስቀል በዓል ከዋዜማው ወይም ከደመራው ጀምሮ በዕለቱም ማኅበረሰቡ ተሰባስቦ በሚያከብርበት ጊዜ በዋናነት የሚቀርብ ምግብ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡
ሁሉም የበዓሉ ተሳታፊዎች እንደየአቅማቸው በየቤታቸው ያለውን አብዚ አዘጋጅተው ይዘው በዓሉ በሚከበርበት ወይም ደመራ ወደ ተለኮሰበት ቦታ በመውሰድ ከባሕላዊ መጠጦች እንደ ጠላ፣ ጠጅ እና አረቂ ጋር እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡አብዚ ከመስቀል በዓል በተጨማሪ በሌሎች ባሕላዊ ክብረ በዓላትም ይቀርባል ነው ያሉት፡፡ ባሕሉ ወደ ትውልድ እየተሻረ ነው ያሉት ወይዘሮ ሊሻንወርቅ ወጣቶች ይሕንን ባሕላዊ ምግብ እንደ እናቶቻቸው እያዘጋጁ እተጠቀሙት ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሚሠራው የማስተዋወቅ ሥራ አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ወለሌ ጌቴ የአብዚ ባሕላዊ ምግብ የብሔረሰቡ መገለጫ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ አብዚ በተለይም በመስቀል በዓል ጊዜ በስፋት ይዘጋጃል ያሉት ተወካይ ኀላፊው ማኅበረሰቡ ለራሱ ከመጠቀም ባለፈ ወደ ገበያ እንዲገባ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ባሕላዊ ምግቡን ለማስተዋወቅ በሆቴሎች እና ሬስቶራንቶች የምግብ ዝርዝር ውስጥ ተካትቶ እንግዶች እንዲጠቀሙት እየተደረገ እንደኾነ ነው የተናገሩት። በተጨማሪም አሠራሩን እና ባሕላዊ እሴቱን እንደጠበቀ ወደ ትውልድ እንዲሻገር ተሰንዶ መያዙንም ገልጸዋል፡፡
አብዚ የብሔረሰቡ ለየት ያለ መገለጫ በመኾኑ በክብረ በዓላት ወቅት በሰፊው እየተዘጋጀ ይቀርባል፤ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮችም አብዚን እና ሌሎች ባሕላዊ ምግቦችን እና መጠጦችን የማስተዋወቅ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ባሕልን መጠበቅ፣ ማልማት እና ለቱሪዝም ግብዓት እንዲውሉ ማድረግ ለማኅበረሰቡ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡ ባሕላዊ ምግብ እና መጠጦች ደግሞ የአንድ ማኅበረሰብ መገለጫ በመኾናቸው በአግባቡ ጠብቆ ለሌላው የማስተዋወቅ ተግባሩ አካል ሊኾን እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!