
ባሕር ዳር: መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ”
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ”
የገጣሚ እና ባለቅኔው መንግሥቱ ለማ ግጥም አደይ ማበብ በጀመረ ቁጥር ትዝ ሳይለን አይቀርም፡፡ ባለቅኔው አደይ አበባ እና የመስቀል ወፍ እንዲህ መስከረምን ጠብቀው የመምጣታቸው ምስጢር ምን እንደኾነ ያጠየቁ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንዲህ በግጥም አስቀመጡት እንጅ የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ ነገር ለማንም ምስጢር ያለው ይመስላል። በዚህ ዙሪያ ሙያዊ አስተያየታቸውን እንዲያካፍሉን የጋበዝናቸው በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ሥነ ጽሑፍ አማርኛ ትምህርት ክፍል ኀላፊ ሒሩት አድማሱ (ዶ.ር) ናቸው፡፡
ዶክተር ሒሩት እንዳሉት ግጥሙ የሚነገርበትን አውድ የሚገልጸው ማኅበረሰብ አለ ይሉናል፡፡ ግጥሙን ለመረዳትም የማኅበረሰቡን ባሕል እና ወግ እንዲሁም አካባቢ ማወቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ በግጥሙ ውስጥ እነዚህ ቃላት ምንድን ነው ያዘሉት ነገር የሚለው ሲታይ የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ ሰው እንደሚቃጠር ሁሉ ተቀጣጥረው እንደሚገናኙ ሰዋዊ የኾነ ባህርይ ተሰጥቷቸው ወቅትን ጠብቀው እንደሚመጡ ይገልጻል ብለዋል፡፡ እነዚህ ፍጥረታት በባህሪያቸው የተለያዩ ናቸው የሚሉት ምሁሯ ወፍ ከእንስሳ ዝርያ ሌላው የአደይ አበባ ደግሞ ከእጽዋት ዝርያ ነውና ለምንድን ነው በወርሐ መስከረም መገናኘት ያስፈለጋቸው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል ብለዋል።
ክረምት እንደሚታወቀው ከችግር፣ ከጨለማ እና ከዝናብ ጋር በተያያዘ አስቸጋሪ ወቅት ነው የሚሉት ዶክተር ሒሩት የዚህን ወቅት ከባድነት ለመግለጽ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ስደታችሁ እና መከራችሁ በክረምት አይሁን” ይላል እና ክረምት ለምንም የሚመች ወቅት አይደለም የሚለውን ለማጠየቅ እንደኾነ አብራርተዋል፡፡ ይሄንን ወቅት አሳልፈን ለፍጥረታቱ ሁሉ ምቹ የኾነውን ጊዜ በተለይም የጨለማውን፣ የችግሩን፣ የጭቃውን ወቅት አሳልፈን የብርሃን፣ የፀሐይ እና የአዲስ ተስፋ የሽግግር ጊዜ ለውጥን ለማመላከት የሚታዩ ኾኖ ነው የምናገኛቸው ይላሉ። የመስቀል ወፍ ቀለሟ ወደ ቀይ የሚያደላ፣ ለእይታ የሚያስደስት ቀለም ያላት ናት። አደይ አበባ ደግሞ በጣም የምታምር የበቀለችበትን ጋራ፣ ተራራ እና ሸንተረር ሳይቀር የምታሸበርቅ ቢጫ አበባ ናት ብለዋል፡፡
ሁለቱም ውብ የኾኑ ዐይነ ግቡ ፍጥረቶች የአዲስ ዓመት ተስፋን የሚያመላካቱ ናቸው ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ የግጥሙ ተናጋሪ የነዚህ ሁለት ነገሮች አብሮ መምጣት ያስደመማቸው ይመስላል ብለዋል። ተፈጥሮን ሥርዓት ባለው መልኩ የሚያነጋግር እንደኾነ ለማሳየት የተጠቀሙበት እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡ እናም ገጣሚው መልስ የያዘ ጥያቄ ነው የጠየቁት ብለዋል። እኛ ተነጋግረን እንደምንግባባው ሁሉ ተፈጥሮ ያሳመራቸው ሁለቱ ፍጥረታት ውስጥ የማናቀው ዓይነት ሥርዓት ያለው ንግግር በተፈጥሮ ውስጥ እንዳለ እና እደተግባቡ ያሳየናል ነው ያሉት ዶክተር ሒሩት፡፡
በሌላ በኩል በነባሩ ባሕል ውስጥ ስናይ ማኅበረሰቡ የሚለው አባባል አለ፤ እሱም ሰው ጠፍቶ ከርሞ ከኾነ ጊዜ በኋላ ሲመጣ “የመስቀል ወፍ ኾንክ” ይባላል እናም የመስቀል ወፍም በሁሉም ጊዜ፣ ቦታ እና ወቅት አትገኝም፤ ይልቁንም በአመዛኙ የመስቀል በዓል በሚከበርበት ወቅት የመምጣት ነገር ነው ያላት ብለዋል።
አደይ አበባም መስከረም ሲጀምር አካባቢ የተወሰነ ይታይ እና በተለይም መስከረም አጋማሽ ላይ በብዛት ይፈካል፤ ምድርም በዛ ቀለም ያሸበርቃል። ወፏም በወርሐ መስከረም መስቀል በዓል አካባቢ የምትገኝ እንዲሁም ደግሞ አበባውም በዚሁ ጊዜ ፈክቶ ምድርን በቀለሙ የሚያስውብ መኾኑ ጊዜው ለእነዚህ ፍጥረታት ምቹ መኾኑን ያሳየናል ነው ያሉት። ከዚህ በተጨማሪ በተፈጥሮ ውስጥ ያለ ምስጢራዊ ንግግር ወቅትን እና ጊዜን ተረድቶ መገኘት እና ከጊዜ ውጭ አለመታየትን የሚያሳይ አንዱ በዚህ ግጥም ውስጥ የምናገኘው ሃሳብ ነው ብለውናል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የወቅት መፈራረቅ ለእንስሳትም ኾነ ለእጽዋት መገኘት፤ እንደገና ለመጥፋትም ጭምር ምክንያት እንደኾነ የሚያመላክትም እንደኾነ ነው ያብራሩት።ስለዚህ የጊዜ መቀየርን፤ የዘመን መለዋወጥን እና አዲስ ጊዜ መምጣትን ለማብሰር ወይም ለመንገር የተፈጠሩ ፍጥረታት እንደኾኑ በባሕሉ ውስጥ ልናየው እንችላለን ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!