
ባሕር ዳር: መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል ደመራ አበራር ሥነ ሥርዓት በአንዳንድ አካባቢዎች መስከረም 16 ደመራው ይበራል።
በሰሜኑ የሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በንግሥት እሌኒ ዘመን አይሁዳውያን የቀበሩትን የክርስቶስ መስቀል ደመራ ለኩሰው ያገኙበት ቀን መስከረም 17 ላይ ደመራ ይለኮሳል። የጎንደር ነገሥታት ክርስቶስ ንጉሠ ነገሥትነቱን እና ሊቀ ካህንነቱን የገለጸበትን የመስቀል በዓል እያከበሩ መጥተዋል። በዓሉ የከተማይቱ ዋና አደባባይ በነበረው ጃንተከል ዋርካ ወይም በፊት በር ከመስከረም 16 ጀምሮ ሲከበር ቆይቷል። የክርስቶስ ንጉሠ ነገሥትነቱ የተገለጸበት መስቀል ደመራ የሚደመረው ደግሞ በንጉሠ ነገሥቱ አዛዥነት ነበር። በዚህም አጼ ደመራ ወይንም አጼ መስቀል የሚለውን ስያሜ እንዲያገኝ አድርጎታል። የንጉሠ ነገሥቱ ደመራ እንደማለት ነው።
ይህ ታሪካዊ ሥፍራ በወቅቱ የመስቀል በዓልን ከማክበር ባሻገር አዋጅ ይነገርበታል፤ ሹም ሽር ይፈጸምበታል፤ ለወንጀለኞችም ፍርድ ይሰጥበታል፤ ሊቃውንቱ ጉባኤ ያካሂዱበታል። ከዚህም ባለፈ ለነገሥታቱ ደጅ የሚጠኑበት፣ ባላባቶች ተሰብስበው የተለያዩ ጉዳዮችን የሚመክሩበት ነበር።
በአጠቃላይ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ክንውኖች የሚካሄዱበት ሥፍራ ነበር። ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ የመስቀል በዓል “መስቀል አደባባይ” እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ እንዲከበር ተደርጓል።
በማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተቀዳሚ ሰብሳቢ እና የበዓሉ አቢይ ኮሚቴ አሥተባባሪ ዲያቆን አንዳርጋቸው እንዳለው እንዳሉት በጎንደር በድምቀት ከሚከበሩት በዓላት መስቀል አንዱ ነው። ደመራው የሚበራበት ቀን በ17 ረፋድ ላይ ነው። የመስቀል በዓል ከዋዜማው ጀምሮ የበዓሉ አከባበር በየመንደሩ ባሉ ልጆች በሆያ ሆዬ ጨዋታ እና በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ይደምቃል። እስከ በዓሉ ዕለት ድረስም ይቀጥላል።
የአብነት ተማሪዎችም ከ14 ጀምሮ የቤተክርስቲያን አልባሳትን በመልበስ በየቤቱ እየዙሩ እንኳን አደረሳቹህ ይላሉ። የሰንበት ትምህርት ቤቶች እና ጽዋ ማኅበራት በበዓሉ ቀን የሚቀርቡ መዝሙሮችን፣ ወረብ፣ በገና እና የመሳሰሉ ሃይማኖታዊ ክንውኖች ላይ ቀድመው ይዘጋጃሉ። የአካባቢው ወጣቶች ደግሞ ከበዓሉ በፊት የተጣሉ ካሉ ያስታርቃሉ፤ መስከረም 17 ንጋት ላይ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምዕመናን እንዲሁም የከተማው ተወካይ በደመራው ሥፍራ ይገኛሉ። ጸሎት እና ምህላ ይደርሳል፤ ሊቃውንቱ እና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ዝማሬ ያቀርባሉ።
ዕለቱን በተመለከተ የወንጌል ትምህርት ተሰጥቶ ሊቀ ጳጳሱ ደመራውን ይባርካሉ። የከተማው ከንቲባ ደግሞ የጥንቱን የንጉሰ ነገሥቱን ሚና ወስደው የተባረከውን ደመራ ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመኾን በችቦ ይለኩሳሉ። የተሰበሰበው ሰው ምስጋና ያቀርባል። እናቶችም በእልልታ ያደምቁታል። ደመራው ከተቃጠለ በኋላ የተጸለየበትን እና የተባረከውን አመድ እና ትርኳሽ ሕዝቡ ወደ ቤቱ ይዞ ይሔዳል። በዓሉ ሳይበረዝ በዚህ መንገድ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በድምቀት እየተከበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ወጣቱ ሃይማኖታዊ እሴቱን ማስጠበቅ፣ አንድነትን እና ወንድማማችነትን ማጠናከር፣ ጠቃሚ ባሕሉንም ጠብቆ ለትውል ሊያስተላልፍ ይገባል ብለዋል። በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃ ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አይቸው አዲሱ እንዳሉት
የመስቀል በዓልን ከመስከረም 14 ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቷል። ከተሠሩ ሥራዎች ውስጥ ደግሞ “ህይወት በአብያተ መንግሥት” በሚል መልዕክት በጥንታዊ አብያተ መንግሥታት ውስጥ በጥንቱ ጊዜ የነበረውን የፍርድ ሥርዓት፣ የኪነ ጥበብ፣ የቀጭን ፈታይ መርሃ ግብር በተዋናያን አማካይነት ሲካሄድ ቆይተዋል።
ለደመራው ደግሞ ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመቀናጀት ቅድመ ዝግጅ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል። በጎንደር ደመራው የሚደመረው በ16 ሲኾን የሚለኮሰው ደግሞ በ17 ነው። በ17 የሚለኮስበት ምክንያት ደግሞ በነገሥታቱ ጀምሮ የመጣ መኾኑን ገልጸዋል። በእለቱ የከተማው የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ይከበራል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!