
ባሕር ዳር: መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል ደመራ በዓል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በድምቀት እየተከበረ ነው።
የመስቀል ደመራ በዓል በአደባባይም ኾነ በግቢ ውስጥ ቢከበር የመስቀሉ በረከት ለሁሉም ሰው ይደርሰዋል ያሉት በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በገዳመ ዮርዳኖስ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የመጸሐፍ መምህር እና የስብከተ ወንጌል ኀላፊው ለቤዛ ጥላሁን ናቸው፡፡
መምህሩ በዓለ ደመራው በመስከረም 16ም ኾነ በ17 መከበሩ የመስቀሉን ጸጋ እንደማያሳጣ ገልጸዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ብዙ ተዓምራትን ሲፈጽም በማየታቸው “እኛ በዚህ መስቀል ሰቅለን የገደልነው ሰው ሃጥያተኛ ነው ብለን ነበር፤ እሱ የተሰቀለበት መስቀል ግን ተዓምር እያደረገ ነውና የሰውየው ጽድቅ ሊገለጽ ነው፤ እውነቱም ሊወጣ ነው፤ ስለዚህ ይኼንን መስቀል ማጥፋት አለብን” ብለው ጉድጓድ ቆፍረው መስቀሉን በመቅበር፣ በዚያም ላይ ጥራጊ እና ቆሻሻ በመድፋት እንዲሰወር ጥረዋል ነው ያሉት፡፡ የተሰቀለበት መስቀልም ለ300 ዓመታት ተዳፍኖ መቆየቱን ነው የተናገሩት፡፡
ንግሥት ኢሌኒ መስቀሉ ያለበትን ቦታ የሚጠቁማት ሰው አላገኘችም ነበር ያሉት መምህር ለቤዛ ከአይሁድ መካከል ኪሪያኮስ የሚባለው ሰው “እኔ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በውል ለይቼ ባላውቀውም ከእነዚህ ከሦስቱ ተራራዎች በአንዱ እንደተቀበረ አባቶቻችን ሲያወሩ ሰምቻለሁ፤ ስለዚህ ደመራ ደምረሽ፣ ስሂንሰንድሮስ የሚባለውን ነጭ ዕጣን በማጤስ፣ ጢሱ ወደ ላይ ወጥቶ ተመልሶ ያረፈበት ቦታ ላይ አስቆፍሪው” አላት፤ ኢሌኒም በተባለችው ቦታ አስቆፍራ መስቀሉን አገኘችው በማለት አብራርተዋል፡፡
ኢሌኒ በቁፋሮ ያስወጣችውን መስቀል በጎሎጎታ ቀራኒዮ በሚባለው ሥፍራ ቤተ ክርስቲያን አሠርታ አስቀምጣዋለች በማለት መምህር ለቤዛ የመስቀል ደመራን በዓል አጀማመር ተናግረዋል፡፡ ተደብቆ የነበረውን መስቀል ቆፍረው ያገኙት ሰዎች መስቀሉን ሲያገኙት “ይሄዋ! ይሄዋ!” ማለታቸውን ተከትሎ በኛም ሀገር የመስቀል ደመራ በዓል ሲከበር “እዮሃ! እዮሃ!” ይባላል ነው ያሉት መምህሩ፡፡
በአብዛኞቹ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ የአደባባይ የደመራ በዓል የሚከበረው በመስከረም 16 መኾኑን ያስታወሱት መምህሩ በመስከረም 17 ንጋት ላይ በግቢያቸው እና በአካባቢያቸው ደመራ ደምረው የሚያከብሩ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡ የመስቀል ደመራ በዓል መከበር ያለበት አቅመ ደካሞችን በማገዝ፣ የተራቡትን በማብላት፣ በሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን በመጸለይ እና በመተባበር መንፈስ መኾን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!