
ባሕር ዳር: መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የመስቀል በዓል አንዱ ነው። በዓሉ ከዋዜማው የደመራ ሥርዓት ጀምሮ እስከ ዋናው በዓል ድረስ በአደባባይ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው።
መስቀል በእምነቱ አስተምህሮ ኢየሱስ ክርስቶስ ተዓምራትን የገለጠበት፣ ለሰው ልጅ መዳን ሲል የተሰቀለበት፣ ፍጹም የኾነ ፍቅር የሰጠበት እንደኾነም ይታመናል። ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ሕዝብና አሕዛብን በአንድ አካል ከራሱ ጋር ለማስታረቅ በቀራንዮ ተሰቀለ፣ ወንጀል የሠሩ ሰዎች ብቻ ይሰቀሉበት የነበረው መስቀል ከጌታ ስቅለት በኋላ የመዳን ምልክትም ሆነ። በዚህም ምክንያት መስቀል የነጻነት፣ የመዳን፣ የእርቅ፣ የፍቅርና የዘላለማዊ ህይወት ምልክት መኾኑን ሊቃውንተ ቤተክርስትያን ያስተምራሉ።
በባርነት ይኖር የነበረው የሰው ልጅ በመስቀሉ በተከፈለለት መስዋትነት ነጻነትን ያገኘበት ስለመኾኑም በመጻሕፍት ተገልጿል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን የግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም አሥተዳዳሪ መምህር አባ ብስራተ ገብርኤል ክፍለ ማርያም መሥቀል ለ5ሺህ አምስት መቶ ዘመን ያህል በሰው ልጆች ላይ ተጭኖ የነበረውን ጨለማ ብርሃን ያደረገበት እንደኾነ አብራርተዋል። መምህር አባ ብስራተ ገብርኤል እንደገለጹት ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከወደቀበት መርገም ያድነው ዘንድ ከቅድስት ድንግል ማርያም በራሱ ፈቃድ በመስቀል ላይ ተሰቅሏል፡፡ በስቅለቱም ዲያብሎስን ድል ነሥቶ የሰው ልጅ በሙሉ ከዲያብሎስ ባርነት ፍጹም ነጻ ወጥቶበታል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መዳን ብሎ መከራን ተቀብሏል፤ የእሾህ አክሊል ተደርጎበታል። ነገር ግን የክርስቶስን ደም ግባት እንኳን ሊጋርደው አልቻለም። በቀራንዮ አደባባይ ከሰማይ ዝቅ ከመሬት ከፍ ብሎ መሰቀሉን ነው ያስረዱት። ይህ ሁሉ ተደርጎበት ክርስቶስ ግን “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለት ይቅርታውን ለሰው ልጆች ሁሉ የገለጸበት መኾኑንም አንስተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን አጥፍቶ ህይወትን የሰጠበት፣ ጥልን አጥፍቶ ፍቅርን ያወጀበት መሥቀል ስለመኾኑም አስረድተዋል። በዚህም በቅድስት ቤተክርስትያን አስተምህሮ ክርስቶስ ከመስቀሉ መስቀሉን ከክርስቶስ ለይቶ የሚታይ የአይደለም ብለዋል።
ክርስቶስ ይህንን ሁሉ መከራ እየተቀበለ ድውያንን የፈወሰበት፣ ተዓምራትን ያደረገበ፣ ጭካኔን በይቅርታ ጥላቻን በፍቅር የቀየረበት በመሥቀል መኾኑ “ጥልን በመሥቀሉ ገደለልን” እንላለን ብለዋል ። የክርስቶስ መስቀል ስለ ፍቅር ለሌሎች ዋጋ መክፈልንና ለሰው ልጅ ራስን አሳልፎ መስጠትን እንደሚያስተምር አመላክተዋል። የመሥቀል በዓል በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ሃይማኖታዊ እሴት ስለመኾኑም ነው የጠቆሙት።
ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በምቀኝነት ለረጅም ዘመናት ተደብቆ ቆይቶ እንደነበር አንስተዋል። በኋላ ንግሥት እሌኒ በብዙ ልፋትና ጥረት በጭስ እየተመራች እውነተኛውን መስቀል አግኝተዋለች።
ይህንን መሠረት በማድረግም በየዓመቱ መስከረም 16 ደመራ የሚከበረው የንግስት እሌኒ መስቀሉን ያገኘችበትን ለማሰብ ስለመኾኑም ነግረውናል።የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ደግሞ መስቀሉ የተገኘበት ዕለት መስከረም 17 እንዲከበር በወሰኑት መሰረት በዓሉ በየዓመቱ በዚሁ ቀን እየተከበረ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!