“መስቀሉ በመስቀለኛ ስፍራ”

2
ባሕር ዳር: መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከተራሮች ሁሉ ተመርጣ የከበረች፣ ጥበበኛ ተጨንቆ የሠራት የጥበብ ውጤት የምትመስል ግን የተፈጥሮ ገጸ በረከት በአካል ተገኝተው የተመለከቷት፤ ሁሉ የተደነቁባት ገራሚ ምድር ናት ግሸን ደብረ ከርቤ።
ግሸን ደብረ ከርቤ ከደሴ ከተማ በ76 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአምባሰል ወረዳ ትገኛለች። የግሸን ደብረ ከርቤ አስደማሚ የተፈጥሮ ቅርጽ ያለው ተራራ፣ በተራራው አናት ላይ ደግሞ የመስቀል ቅርጽ ያለው አምባ ነው። የግሸን አምባ ታሪክ ተሠርቶ የተቀመጠበት፣ ነገሥታት የከተሙበት፣ ቅዱሳን ያረፉበት፤ ከጥንት ጀምሮ የሃይማኖት ሥርዓት የተፈጸመበት፣ የታሪክ ማኅደር፣ የሃይማኖት ማዕከል የኾነ ድንቅ ስፍራ ነው። ከተፈጥሮ መልከዓ ምድራዊ አስደናቂነቷ በተጨማሪ የእየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል ያረፈበት የተቀደሰች ስፍራ ስለመኾኗ በግሸን ደብረ ከርቤ ሰበካ ጉባኤ አማካኝነት በታተመውና መጽሐፈ ጤፉት በተሰኘው መጽሐፍ ተገልጿል ።
በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድም ዳግማዊት ኢየሩሳሌም በመባልም ትታወቃለች። ወደ ቦታዋ በመሄድም መንፈሳዊ በረከትን ለማግኘት በርካታ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ይናፍቃሉ፣ ይመኛሉ። የግሸንን ምድር መርገጥ መባረክ እንደኾነም በአማኞች ዘንድ ይገለጻል። በእግር መጓዝ በረከት ነው ብለው ብዙዎቹ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ወደ ግሸን ይዘልቃሉ። ሌሎችም እስከ አምባው ድረስ በመኪና፣ በበቅሎ እየተጓዙ ይሳለማሉ፣ በዓለ ንግሷንም ያከብራሉ። በመጽሐፈ ጤፉት እንደተገለጸው የግሸን ደብረ ከርቤ የተለያየ ዘመን በተለያየ ስያሜ ስትጠራ ኖራለች። ደብረ ነጎድጓድ፣ ደብረ እግዚአብሔር ስትባልም ቆይታለች።
በኋላም በዘመኑ ስፍራው ከሃይማኖት ቦታነቱ በተጨማሪ የአሥተዳደር ቦታ ኾና በማገልገሏ የነገሥታት ልጆች እንዲማሩና በዚያውም እንዲኖሩ በመደረጉ ቦታው ደብረ ነገሥት በመባል እንዲጠራ ሁኗል፡፡ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ከስናር ወደ ኢትዮጵያ አምጥተው በስፍራው ላይ ካሳረፉት በኋላ ደግሞ አምባው የመስቀሉ መገኛ ነው በማለት ስያሜዋ ግሸን ደብረ ከርቤ ተብላለች፡፡ ግሸን መግቢያዋም ኾነ መውጫ በሯ አንድ ብቻ ነው። ይህ ብቸኛው በርም በጣም ጠባብ ነው። በግሸን ደብረ ከርቤ አምስት አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡በግሸን አምባ የተሠራው የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር አብ ይባላል። የተመሠረተውም በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግሥት በ517 ዓ.ም አባ ፈቃደ ክርስቶስ በተባሉ አባት መኾኑን በመጽሐፈ ጤፉት ላይ ተመላክቷል።
በጊዜ ሂደትም የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን በመመሥረት ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሲሰጥባቸው ቆይተዋል። በአሁኑ ሰዓት የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እና የቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን ተጨምረው በግሸን ደብረ ከርቤ ይገኛሉ፡፡ የመስቀል በዓል በግሸን ደብረ ከርቤ በልዩ ኹኔታ ይከበራል። ምክንያቱ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ አደባባይ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል የሚገኝበት ስፍራ በመኾኑ ነው። የግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም አሥተዳዳሪ መምህር አባ ብስራተ ገብርዔል ክፍለ ማርያም መስቀሉ ሲታሰብ ግሸንም አብራ እንደምትነሳ ይገልጻሉ። ግሸን ደብረ ከርቤ ክርስቶስ ስጋውን እና ደሙን የፈተተበት ግማደ መሥቀል ያረፈበት መስቀለኛ ስፍራ ስለመኾኑ አስረድተዋል። ስለ ግሸን መስቀለኛነትም ቦታው ራሱ ይናገራል ይላሉ።
ለአጼ ዘርዓ ያዕቆብ መስቀሉን በመስቀለኛ ቦታ እንዲያስቀምጥ በተገለጠለት ራዕይ መሠረት ግማደ መስቀሉ በመስቀለኛዋ ቦታ በግሸን መቀመጡንም ነው ያብራሩት። በኢትዮጵያ እንደ ግሸን አይነት የመስቀል ቅርጽ ያለው ቦታ የለም ያሉት አባ ብስራተ ገብርኤል የመስቀል በዓል አከባበሩም ይህንን መነሻ መሠረት ባደረገ መልኩ እንደሚከበር አመላክተዋል። የመስቀል ክብረ በዓልም በርካታ ምዕመናን ከሩቅም ከቅርብም በመሠባሠብ እንደሚያከብሩትም አንስተዋል። አባ ብስራተ ገብርኤል እንደሚሉት መስቀልን የክርስቶስ ግማደ መስቀሉ ባለበት በግሸን ማክበር በረከትን እንደሚያስገኝ ጠቁመዋል።
ይህንን መነሻ በመረዳትም በርካታ ምዕመናን ወደ ስፍራው እየመጡ እንደሚያከብሩት ነው የተናገሩት። በ16 ደመራ በመደመር እና በመለኮስ የመስቀሉን መገኘት የሚያሳይ ሥርዓት በመከወን እንደሚከበር ነው የገለጹት።በ17 ደግሞ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ተሰባስበው በልዩ ልዩ መርሐ ግብር እና ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት እንደሚከበርም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየመስቀል በዓል እና የፊፊ ባሕላዊ ጨዋታ- በጃዊ
Next article“ጥልን በመሥቀሉ ገደለልን”