
ባሕር ዳር፡ መስከረም 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል ሃይማኖታዊ በዓል በባሕላዊ ትውፊት ታጅቦ ከሚከበርባቻው አካባቢዎች ውስጥ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ይገኝበታል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በፊፊ ባሕላዊ ጨዋታ ታጅቦ በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች ውስጥ የጃዊ ወረዳ ቀዳሚው ነው። በዓሉም ከዋዜማው ጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የራሱ የኾኑ ሂደተቶችን ያልፋል። በአካባቢው ማኅበረሰቡ በተደራጀ መንገድ በዓሉን ለማክበር አማካይ የኾነ ቦታ ይመረጣል። በሥነ ምግባሩ የተመሠገነ፣ ይቅር ባይ እና በደመራ ተከላ ለሚሳተፉት ሰዎች የሚያስፈልገውን ድግስ የማዘጋጀት አቅም ያለው አንድ አሥተባባሪ (ደመራ ተካይ) ከማኅበረሰቡ ይመረጣል። ደመራ ተካዩ የተለያዩ ችግሮች ካላጋጠመው ወይም ደግሞ በፍላጎት በቃኝ ካላለ በስተቀር ኀላፊነቱን ይዞ ይቀጥላል።
የመስቀል በዓል ከመድረሱ ትንሽ ቀደም ብሎ የአካባቢው ወጣቶች እንጨት ሠብሥበው በየቤታቸው ያስቀምጣሉ፡፡መስከረም 16 ቀን ደግሞ በየቤቱ አባወራው የደመራውን ችቦ ያሥራል። የደመራ ተከላ ሰዓቱ ሲደርስም በአካባቢው የተመረጠው ደመራ ተካይ ማኅበረሰቡ እንዲሠባሠብ በጡሩምባ ጥሪ ያስተላልፋል። ማኅበረሰቡም የደመራ እንጨት በመያዝ ወደ ደመራ መትከያ ቦታ ይሠባሠባል። የተመረጠው ደመራ ተካይም “እዮሃ” እያለ የደመራዋን ዋና ቋሚ ወይንም ምሰሶ መጀመሪያ ከተከለ በኋላ ሌሎችም ያመጡትን እንጨት በጋራ በመኾን ደመራውን ያቆማሉ። ደመራው ተደምሮ እንደተጠናቀቀ በደመራ ተከላው የተገኙት ሰዎች በአራቱ አቅጣጫ አየዞሩ ፈጣሪያቸውን አመሥግነው መሬት ስመው ይቀመጣሉ።
ባለ ግርማ ሞገሶቹ ጉምቱ የአካባቢው ሀገር ሽማግሌዎች ተነስተው ይመርቃሉ፡፡ከተመረቀ በኋላ “እዮሃ” እየተባለ ደመራውን ዞረው ካበቁ በኋላ እየጨፈሩ ወደ ደመራ ተካዩ ቤት ይሄዳሉ። ከደመራ ተካዩ ቤት እንደደረሱም የተዘጋጀውን ባሕላዊ ምግብ እና መጠጥ እየቀማመሱ የልብ የልባቸውን ይጨዋወታሉ። ከንጋቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ደግሞ ችቦውን በመለኮስ በጡሩምባ በማድመቅ ወደ ደመራ ቦታ ይጓዛሉ፡፡ ደመራው ላይ ሁሉም ሰው ሲሠባሠብ ሽማግሌዎች ይመርቃሉ። ከምረቃ በኋላ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ፊታቸውን አዙረው ችቦውን በማቀጣጠል ደመራው ይለኮሳል።
መስከረም 17 በደመራው ቦታ የተመራጩ ደመራ ተካይ ባለቤት ያዘጋጀችውን ምግብ እና መጠጥ ቀድማ ለተሠበሠበው ሰው ታቀርባለች፡፡ የተሠበሠቡ ሰዎችም ፈጣሪያቸውን እያመሠገኑ የተደገሰውን ድግስ በጋራ ኾነው ይመገባሉ። በደመራው የተሳተፉ ሌሎች ሰዎችም በቤታቸው ያዘጋጁትን ምግብ እና መጠጥ እያቀረቡ በዓሉን በተለያዩ ጨዋታዎች ያሳልፋሉ። በዓሉ ከሚደምቅባቸው መንገዶች መካከል ደግሞ የፊፊ ባሕላዊ ጨዋታ አንዱ ነው። የፊፊ ባሕላዊ ጨዋታ ከሐምሌ መጨረሻ እስከ መስከረም 20 የሚከበር ባሕላዊ ጭፈራ ቢኾንም ከመስቀል ዋዜማ ጀምሮ ደግሞ በልዩ ድምቀት እንደሚከናወን በጃዊ ወረዳ ነዋሪ የኾነው ወጣት ጌትነት ምትኩ ገልጾልናል።
በተለይም ደግሞ ደመራው ከተለኮሰ በኋላ ከወጣት እስከ አዛውንት በባሕላዊ አለባበስ ታጅበው የተዘጋጀውን ድግስ እየተመገቡ በባሕላዊ ጨዋታ በዓሉን ያደምቁታል። ወደ ምሽት በበዓሉ ላይ የዋለው ሰው ሁሉ በጋራ ኾኖ እየጨፈረ የደመራ ተከላ መሪ ኾኖ ወደ ተመረጠው ሰው (ደመራ ተካይ) ቤት ጉዞ ያደረጋል፡፡ ከደመራ ተካዩ ቤት ከተገባ በኋላም የተዘጋጀው ድግስ እየተበላ እና እየተጠጣ ጨዋታው ይቀጥላል፡፡
እስከ መስከረም 19 ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች እና ጭፈራዎች ዝግጅቱ ይቀጥላል። መስከረም 19 ቀን ደግሞ ወጣቶች ፊፊ እየተጫወቱ በየቤቱ በመዞር ገንዘብ ይቀበላሉ።
በተሠበሠበው ገንዘብ ፍየል ተገዝቶ አስፈላጊው ሁሉ ከተዘጋጀ በኋላ መስተንግዶ ተከናወኖ “ለቀጣይ ዓመት በሰላም ያድርሰን” እየተባለ ተመራርቆ በዓሉ ይጠናቀቃል። የመስቀል በዓል ሲከበርም መከባበርን፣ ሰላምን መስበክ፣ አንድነትን ማጠናከር ዋነኛው ትኩረት ነው። ለቂም እና ጥላቻ ጊዜ እና ቦታ መስጠት ላይ በዓሉ ከመድረሱ በፊት የተጣሉ ሁሉ ከልባቸው እርቅ ይፈጽማሉ። በመስቀል በዓል የታረቁ ሰዎችም እርቃቸው የጸና መኾኑን ገልጸውልናል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ወለሌ ጌቴ የመስቀል በዓል በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በተለይም ደግሞ ጃዊን ጨምሮ በቆላማ አካባቢዎች ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ትውፊቱን ጠብቆ ይከበራል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ መስከረም 16 በከተማ ይደመርና መስከረም 17 ቀን ከ12 ሰዓት ጀምሮ ደግሞ በየመንደሩ ማኅበረሰቡ በቡድን በመኾን ደመራው ይደመራል። ከደመራው በኋላ እርድ ይፈጸማል፤ ባሕላዊ መጠጥ እና ምግብ ቀርቦ በጋራ በመኾን መስተንግዶ ይከናወናል። በዓሉ ካለፈ በኋላ እስከ ታኅሣሥ 30 በወር በተወሰኑ ቀናት ማኅበረሰቡ በየተራ ይገባበዛል። በዓሉ በጃዊ እና በአንዳንድ አካባቢዎች በፊፊ ባሕላዊ ጨዋታ ስለሚታጀብ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል። የፊፊ ጨዋታ ሴቶች በአደባባይ ወጥተው ከወንዶች ጋር የሚጫወቱበት ባሕላዊ ጨዋታ በመኾኑ የሴቶችን እኩልነት ያረጋገጠ እንደኾነ ይታሰባል። የመስቀል በዓል መከባበር፣ ሰላም እና ፍቅር የሚሰበክበት እና አንድነት የሚጠናከርበት መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!