”የመስቀል በዓል ከፈተና በኋላ ድል እና መነሳት መኖሩን ያስተምራል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

10
ባሕር ዳር: መስከረም 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል ደመራ በዓል በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም መስቀል አደባባይ እየተከበረ ነው።
በሥነ ሥርዓቱ የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሃም እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ተገኝተዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በበዓሉ ባስተላለፉት መልዕክት ለባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን እና በዓለም ላይ ለሚገኙ የበዓሉ አክባሪዎች እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል። የመስቀሉ በዓል ከፈተና በኋላ ድል ከመውደቅ በኋላ መነሳት መኖሩን ያሳየናል ያሉት አቶ ጎሹ የመስቀል በዓል እንደገና የመገለጥ እና የመነሳት ነው ብለዋል።
ሀገር በፈተና ውስጥ ብትኾንም እንደ መስቀሉ ሁሉ የመነሳቷን አይቀሬነት ገልጸዋል። ያጋጠመን ሁኔታ ፈተና የበዛበት ቢኾንም ከፈተና በኋላ ድል እንዳለ አምነን እያለፍነው ነው። በጽኑ አቋም ከሕዝባችን ጋር ሰላማችን አስከብረንም እንቀጥላለን ብለዋል። የዘንድሮው የመስቀል በዓላችን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተመርቆ በተበሰረበት ማግስት ነው። በቀጣይም ሀገራችን ፍላጎቷን እየጠየቀች እና እያገኘች ትቀጥላለች። ይህንን በዓል ነገም በድል ላይ ኾነን እናከብረዋለን፤ ለዚህም ውስጣዊ አንድነታችን እና ሰላማችን መጠበቅ ያስፈልገናል ብለዋል።
በሰላም እጦት ምክንያት የምንጎዳው እኛው መኾናችን አውቀን የሌላ አካልን ጣልቃ ገብነት ሳንጠብቅ ችግሮችን እኛው ራሳችን እንፍታ ያሉት ከንቲባ ጎሹ የሰላም ጥሪው ለሁሉም ነውና መገዳደል እና ደም መፋሰስ ይቁም ብለዋል። በሰላም የምንመላለስበት ዘመን እንዲኾንልን እንሠራ ነው ያሉት። በቀጣይ ወራት ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት በከተማዋ በድምቀት እንደሚከበሩ ጠቅሰው የጥር ጊዮርጊስ የባሕር ዳር ልጆች እና እንግዶች መጥተው እንዲያከብሩም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በዓላትን ስናከብር እሴቶቻችን አክብረን በመከባበር መኾን አለበት፤ የተጎዳውን እሴታችን ጠግነን መኾን አለበት ብለዋል። እንደዛሬው ሁሉ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በዓላት በሰላም እንዲከበሩ አስተዋጽኦዋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል።
የከተማው ሕዝብም ለበዓላት ድምቀት ለሚያደርገው ትብብር አመስግነዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“መስቀል ፍቅር እና አንድነት የተገኘበት፣ ጥል የተሸነፈበት፣ እርቅ የታወጀበት ነው” ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ
Next articleየመስቀል በዓል እና የፊፊ ባሕላዊ ጨዋታ- በጃዊ