የመስቀልን በዓል የቱሪዝም ፍሰቱን በሚጠብቅ ሥርዓት ማክበር ይገባል።

14
ባሕርዳር፡ መስከረም 16 /2018ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡
በዓሉ በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት እና በባሕላዊ ትውፊቶች ታጅቦ ነው የሚከበረው። በመስቀል በዓል ደመራ መደመር እና መለኮስ የሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እንዱ አካል ነው። ደመራው እንደተለኮሰ ምዕምናን “እዮሃ አበባየ መስከረም ጠባየ” በማለት ደመራውን እየዞሩ ለበዓሉ ያላቸውን ክብር ይገልጻሉ፤ ለበዓሉ በመድረሳቸው ፈጣሪን ያመሠግናሉ፤ መጭው ዘመንም የሰላም እና የጤና እንዲኾንላቸው ይመኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አስተምህሮ መሠረት የመስቀል በዓል ንግሥት እሌኒ በኢየሩሳሌም ቀራኒዮ ጎሎጎታ በሚባል ቦታ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት ቁፋሮ ያስጀመረችበትን ቀን ለማሰብ የሚከበር በዓል ነው፡፡
ይህ ታላቅ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል በሚገኝበት በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ግሸን ደብረ ከርቤ በድምቀት እንደሚከበር ከክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ በርካታ ባሕላዊ ክዋኔዎችን አካቶ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል እንደየ አካባቢው በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ነው የሚከበረው። በዓሉ ደመራ በመደመር፣ ጧፍ በማብራት፣ አደይ አበባ በመያዝ፣ ደቦት(ችቦ) በማብራት፣ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ ዝማሬዎችን በማሰማት እና ባሕላዊ አልባሳትን በመልበስ ይከበራል፡፡ ይህ ሥርዓት እና ትዕይንት ደግሞ ጎብኝዎችን የሚስብ ነው፡፡
የመስቀል በዓል አከባበር ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ዓለም አቀፍ ቅርስነት በ2006 ዓ.ም ተመዝግቧል፡፡ በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ መመዝገቡ ቅርሱን የተመለከቱ መረጃዎች በድርጅቱ ድረ ገጽ ላይ እንዲለቀቅ ዕድል የሚፈጥር በመኾኑ ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኝ ያደርጋል። ይህ ደግሞ በተለይም የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ስለበዓሉ በቂ መረጃ እንዲኖራቸው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ያግዛል። ይህ በዓል የቱሪዝም መስህብ በመኾኑ ከቀድሞ በተሻለ እንክብካቤ እንዲደረግለት እና ለትውልድ እንዲተላለፍም የሚጠቅም ነው፤ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችን መሳቡም ሌላው የበዓሉ ገጸ በረከት ነው፡፡
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበበ እምቢያለ በዓሉ በአማራ ክልል ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ መካከል በዓላት አንዱ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የመስቀል በዓል በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በአደባባይ በድምቀት የሚከበር በዓል እንደኾነም ገልጸዋል።
በዓሉ ለቱሪዝም ከፍተኛ የኾነ ፋይዳ ያለው የማይዳሰስ ዓለም አቀፍ ቅርስ ነው ያሉት ኀላፊው እንደ ክልል በሁሉም አካባቢ በድምቀት ቢከበርም በግሸን ደብረ ከርቤ ደግሞ በልዩ ሁኔታ ይከበራል ብለዋል፡፡ ለዚህም ቀደም ብሎ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡
ለክብረ በዓሉ ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች የሚሄዱበት በመኾኑ በተለይም ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም መነቃቃት ፋይዳው የጎላ መኾኑን አንስተዋል፡፡
በበዓሉም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ እና ከዚህም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ይገኛል ተብሎ መታሰቡንም ጠቁመዋል፡፡ የቱሪዝም ዘርፉን አስተማማኝ ለማድረግ በሀገር ውስጥ ቱሪዝም ላይ መመስረት መቻል አለበትም ብለዋል፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባለፈ ማኅበራዊ ትስስር የሚፈጥር ነውም ብለዋል፡፡ ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶች ጎን ለጎን ሌሎች በአካባቢው የሚገኙ የመስህብ ሃብቶችን እንዲጎበኙ ያስችላል ነው ያሉት፡፡ ጎብኝዎች ወደ ግሸን ሲመጡ ደሴ ላይ በሚያድሩበት ጊዜ በደሴ እና አካባቢው ያሉትን የቱሪዝም ስፍራዎች እንዲጎበኙ ምቹ ኹኔታ እንደሚፈጥርም ገልጸዋል፡፡ የመስቀል በዓል የአደባባይ እና በጋራ የሚከበር በዓል ነው ያሉት ኀላፊው ማኅበረሰቡ በጋራ በየአካባቢው ያለውን ነገር የሚበላበት፣ የሚጠጣበት፣ ወጣቶች ችቦ እያበሩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ዜማዎችን በማዜም የሚጫወቱበት በመኾኑ ወንድማማችነት እና እህትማማችነትን የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶች ከማኅበረሰቡ ጋር በጋራ የሚከውኑት ተግባር የጋራ እሴቶችን እና አብሮነትን የሚያጠናክር መኾኑንም ነው የገለጹት፡፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችም ጎብኝዎች በጉዞ ማኅበር እና በግል ወደ ግሸን እንደሚገቡም ተናግረዋል። እንደ ቱሪዝም ሲታሰብ የመስቀል በዓል ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ የመስቀል በዓል በሚከበርበት ጊዜ ባሕላዊ አልባሳትን በመልበስ የሚከበርም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ማኅበረሰቡን ወደራሱ እሴት በመመለስ በዘመናዊነት ሰበብ ባሕሉ እንዳይዋጥ ያግዛል ነው ያሉት፡፡ የባሕል ልብስ በራሳችን የሚመረት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣ ነው፤ ለዚህም እንደ መስቀል አይነት በዓላት ማኅበረሰቡ በባሕል አልባሳት የሚዋብበት በመኾኑ የቱሪስቶችን ቀልብ ይሥባል ነው ያሉት፡፡
በዓሉ ባሕላዊ ዕሴቱን እንደጠበቀ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ እና ማኅበረሰቡ ፍቅር በተሞላበት መንገድ እንዲያከብረው የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የጥናት ሥራዎች እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ይህም የሚስተካከሉትን ለማስተካከል እና የሚያድጉትን ዕሴቶች ለማሳደግ እንደሚጠቅም ነው ያስገነዘቡት፡፡ የሃይማኖት አባቶችም በዓሉ ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር እየሠሩ ነው፤ ለዚህም ቢሮው ከሃይማኖት አባቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ኮሚቴ አዋቅሮ በጋራ እንደሚሠራ ነው የገለጹት፡፡ በጋራ መሠራቱም በዓላት የቱሪዝም መስህብ ኾነው ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ እንዲኖራቸው ያስችላል ነው ያሉት፡፡
የመስቀል በዓል ዓለም አቀፍ ቅርስ ኾኖ የተመዘገበው ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ዕሴቶቹ አስተማሪነት ያላቸው በመኾናቸው መሟላት ያለበትን መስፈርት አሟልቶ ነው ብለዋል፡፡የተመዘገቡ መስፈርቶችንም ማስጠበቅ ይገባል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ በዓሉን ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ ፍቅር በተሞላበት መንገድ በማክበር ለቱሪዝም ያለውን አስተዋጽኦ ከፍ እንዲያደርግም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleእግዚአብሔር ከኛ የሚፈልገው ሰላማዊነትን እና ይቅርባይነትን ነው።
Next articleየመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል ዓደባባይ በድምቀት እየተከበረ ነው።