
ባሕር ዳር: መስከረም 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል ደመራ ሥነ ሥርዓት በባሕር ዳር ከተማ በምስከየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ዓደባባይ እየተከበረ ነው።
በሥነ ሥርዓቱ የተገኙት እና አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ ምዕመናን በዓሉ የፍቅር በመኾኑ በፍቅር እና በመተሳሰብ ልናከብረው ይገባል ብለዋል። የበዓሉ ተሳታፊ መምህር ሙሉአዳም ታምሩ ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል። የደመራ በዓል ላይ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና መዘምራን ስለ መስቀሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ነው ብለዋል። ምዕመኑ ከየአቅጣጫው ተሰባስበው በመዝሙር እና ሽብሸባ እያከበሩት እንደኾነ ነው የገለጹት።
መስቀል ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት እና መዳን የሚሰበክበት በዓል መኾኑን የጠቀሱት መምህር ሙሉአዳም በበዓሉ የሰው ልጅ በፍቅር እና በይቅርታ ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖር እናስተምርበታለን ነው ያሉት። ክርስቶስ ያከበረውን መስቀል ስናከብር ሰላምን ፍቅርን ይቅርታን እናገኝበታለን ብለዋል። “እግዚአብሔር ከኛ የሚፈልገው ሰላማዊነትን እና ይቅርባይነትን ነውና” ይህንን በተግባር መፈጸም ይጠበቅብናል ብለዋል። የመስቀል በዓል ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች መካከል አንዱ በመኾኑ ዓለም እየተከታተለው እንደኾነም ገልጸዋል። ኢትዮጵያውያንም በዓሉን በፍቅር እና በአንድነት በማክበር ለዓለም ሰላምን እና ፍቅርን ማስተላለፍ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ሌላኛዋ የሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ምንታምር ጌቴ መስቀሉ ድኅነታችን፣ አርማችን እና ምልክታችን ስለኾነ ከየቤተ ክርስቲያኑ እና ከየደብራችን ተነስተን ወደ በዓሉ ዓደባባይ መጥተናል ብለዋል። የመስቀል በዓልን ስናከብር በደስታ፣ በፍቅር እና በምስጋና መኾን አለበት ነው ያሉት። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ፍቅር ሲል ተሰቅሎበት የሰጠንን መስቀል ትምህርት ወስደን በዓሉን በሰላም፣ በፍቅር እና በአንድነት ልናከብረው ይገባል ብለዋል። ሁሉ ያልጎደለበት አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከልዕልናው ወርዶ በጠባብ ደረት፣ በአጭር ቁመት ተወስኖ የተወለደው ስለ ፍቅር ሲል ነው ብለዋል። እኛም ሀገራችን ያጋጠማትን ችግር በማሰብ በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን እያሰብን ሊኾን እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!