ደመራ ሌላው የኢትዮጵያ መልክ!

5
ባሕር ዳር፡ መስከረም 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ መስከረም 16 የደመራ በዓል ይከበራል። መስከረም 17 ደግሞ የመስቀል በዓል ሥርዓት ይከናዎናል። ለመኾኑ “ደመራ ማለት ምን ማለት ነው?”ስንል በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ አሥተዳደር ዞን አምባሰል ወረዳ የምትገኘው የግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም ዋና አሥተዳዳሪ መምህር አባ ብሥራተ ገብርኤል ከፍለማርያምን ጠይቀናል።
እሳቸውም በተለይም በግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም መስከረም 16 ደመራ ተለኩሶ ይበራል። መስከረም 17 ደግሞ ቅዳሴ ተቀድሶ የመስቀል በዓል ሥርዓት ይፈጸማል ነው ያሉት። “ደመራ” የሚለው ቃል ደመረ፤ ጨመረ፤ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተወሰደ መኾኑን ተናግረዋል።
መምህር አባ ብሥራተ ገብርኤል ደመራ መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሠብሠብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን ፣ አንድነትን እና ኅብረትን ያመለክታል ነው ያሉት፡፡
በ33 ዓመት ከሦስትወሩ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስ በስቅለቱም ዲያብሎስን ድል ነሥቶ በሲዖል ለነበሩ ነፍሳት ነጻነትን እንደሰበከላቸውና የሰው ልጅም በሙሉ ከዲያብሎስ ባርነት ፍጹም ነጻ መውጣቱን መምህር አባ ብሥራተ ገብርኤል አብራርተዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ተዓምራትን በማድረጉ የታወኩ አይሁዳውያን መስቀሉን ከሰዎች ዕይታ ለመሰወር ወሰኑ። ጉድጓድ ቆፍረውም ቀበሩት ነው ያሉት። አይሁዳውያን መስቀሉን በቀበሩበት ቦታ ለ300 ዓመታት ያህል የቆሻሻ መጣያ እና ማከማቻም እንዳደረጉት ነው መምህር አባ ብሥራተ ገብርኤል የገለጹት።
አይሁድ ለጊዜው መስቀሉን ከዐይን ቢሰውሩትም ከክርስቲያኖች ልቦና ግን ሊያወጡት አልቻለም ያሉት አባ ብሥራተ ገብርኤል የመስቀሉ ብርሃን በልቦናቸው የሚያበራ ክርስቲያኖች እየበዙ መምጣታቸውን ገልጸዋል። መስቀሉንም መፈለግ መጀመራቸውን በመጠቆም። ንግሥት ኢሌኒም መስቀሉን ከተቀበረበት ለማውጣት በ327 ዓ.ም ወደ ኢየሩሳሌም መሄዷን ነው መምህር አባ ብሥራተ ገብርኤል የተናገሩት።
ንግሥት ኢሌኒ እንደደረሰችም ስለ ክብረ መስቀሉ መረመረች፤ ጠየቀች፡፡ ቦታውን የሚያስረዳት ግን አላገኘችም ነው ያሉት፡፡ አይሁድ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ለማሳየት ባይፈልጉም በኋላ ባደረገችው ጥረት አረጋዊው ኪራኮስ የጎልጎታን ኮረብታ አመላከታት፤ ዳሩ ግን ኪራኮስ ዘመኑ ከመርዘሙ ጋር ተያይዞ በአካባቢው ከነበሩት ከሦስቱ ተራሮች ውስጥ መስቀሉ የሚገኝበት የትኛው እንደኾነ ለይቶ ማወቅ አልቻለም ብለዋል፡፡
ንግሥቲቱ ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደኾነ ለመለየት በእግዚአብሔር መልአክ እርዳታ ደመራ አስደመረች። እጣን ጨምራ በማቃጠል ጸሎት ተያዘ፡፡ የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ በመውጣት በቀጥታ ተመልሶ መስቀሉ ባለበት ተራራ ላይ በማረፍ እና በመስገድ መስቀሉ ያለበትን ትክክለኛ ሥፍራ አመለከታት፡፡ መስከረም 17 ቀን ቁፋሮው እንዲጀመርም አዘዘች፡፡ ደመራም ተደመረ ብለዋል።
መስቀሉ ከተገኘ በኋላ ንግሥት ኢሌኒ እና ክርስቲያኖች ኹሉ ለመስቀሉ ሰገዱለት፡፡ በየሀገሩ ያሉ ክርስትያኖችም ኹሉ የመስቀሉን መገኘት በሰሙ ጊዜ መብራት አብርተው ደስታቸውን በመግለጽ ለዓለም እንዲታወቅ አደረጉ፡፡ ንግሥት ኢሌኒም ለመስቀሉ ቤተ መቅደስ ከሠራችለት ጊዜ ጀምሮ መስከረም 17 ቀን የመስቀል በዓል በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት እየተከበረ እንደሚገኝ ነው የግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም ዋና አሥተዳዳሪ መምህር አባ ብሥራተ ገብርኤል ከፍለማርያም የተናገሩት።
እንደ መውጫ
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ድረ ገጽ እንዳስነበበው ንግሥት ኢሌኒ ለዓመታት የጓጓችለት መስቀል ወጥቶ ባየችው ጊዜ ልጇን ‹‹እዮሃ!›› “አበባዬ! መስቀሉን እየዋ! እኔም አየሁታ” እንዳለችው አትቷል። ደመራ እና መስቀል የአንድነት፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የአብሮነት፣ የምሥጋና እና የተስፋ እሴቶች የሚገለጹበት ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓል ነው። እኛም በዓሉ ላይ ኾነን ግጭቶች የሚመክኑበት፣ ቂም እና ጥላቻ የሚወገዱበት፣ በጎ ዜና የሚደመጥበት እንዲኾን ምኞታችን ከልብ ነው።
መልካም የደመራ በዓል!
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጸጥታ መዋቅሩ ውጤታማ ተግባራትን እንዲያከናውን የሕዝብ ድጋፍ ያስፈልገዋል።
Next articleየምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት