
ሁመራ፡ መስከረም 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለሰላም እና ልማት ውጤታማነት መንግሥት እና ሕዝብ ተቆራኝተው መሥራት እንዳለባቸው በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የአካባቢውን ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ በማስመልከት የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር እና በዙሪያው የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በጋራ ውይይት አድርገዋል። የጸጥታ አካላት የሕዝቡን ሰላም ለመጠበቅ ሲባል ለሚከፍሉት ዋጋ እውቅና መስጠት እንደሚገባ የመድረኩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል። ሕዝብ እና መንግሥት ለሰላም እና ለልማት በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም አንስተዋል።
የሕዝቡን ሰላም የሚያውኩ፣ በሕገ ወጥ ተግባራት ላይም በሚሳተፉ አካላት ላይ መንግሥት ቁርጠኛ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ነው ነዋሪዎቹ የጠቆሙት። በዚህም ኅብረተሰቡ የበኩሉን መወጣት አለበት ብለዋል። የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማጽናት የሕዝብ ተሳትፎ ሚናው ከፍተኛ በመኾኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የተናገሩት የከተማ አሥተዳደሩ ከንቲባ አብዱልዋሀብ ማሙ ናቸው። ከሕዝብ የሚሰወር ነገር የለም ያሉት ከንቲባው “የጸጥታ መዋቅሩ ውጤታማ ተግባራትን እንዲያከናውን የሕዝብ ድጋፍ ያስፈልገዋል” ብለዋል።
ሥርዓት አልበኝነትን ለማስወገድ በቅንጅት መሥራት ይገባል ያሉት ደግሞ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ወለላው ተገኘ ናቸው። የጸጥታ አካላትም ኀላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ሕገ ወጥ የሰዎች እና የመሳሪያ ዝውውር ለሕዝቡም ኾነ ለመንግሥት ሕልውና አደገኛ መኾኑንም ገልጸዋል። ይሄን ለመከላከልም ጥብቅ ቁጥጥር እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የጸጥታ መዋቅሩ ለሕዝብ አገልግሎት የቆመ መኾኑን የተናገሩት የዞኑ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ እና የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ተወካይ ጌታቸው ሙሉጌታ ናቸው። የጸጥታ አካላት ሕዝባቸውን በቅንነት እና በከፍተኛ የኀላፊነት ስሜት መጠበቅ እና ማገልገል ቁልፍ ተግባራቸው እንደኾነም አንስተዋል።አካባቢው ያልተመለሰ የወሰን እና የማንነት ጥያቄ ያለበት በመኾኑ የጸጥታ መዋቅሩ ይሄንን ታሳቢ ማድረግ አለበት ብለዋል። ሕገ ወጥ ተግባራትን በሚፈጽሙ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንደሚገባም በውይይቱ ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!