የወባ ሥርጭትን ለመቀነስ ሁሉም መከላከል ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል።

8
ባሕርዳር፡ መስከረም 16 /2018ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ዓመታት ወባ ላይ በተሠራው ሥራ ከአስሩ ለሞት አደጋ ምክንያት ከኾኑ በሽታዎች ውጭ ማድረግ ቢቻልም ባለፉት ሦሥት ዓመታት በሽታው እየጨመረ ይገኛል።
በ2017 በጀት ዓመት ብቻም ከ2 ሚሊዮን በላይ የወባ ሕሙማንን ማከም ተችሏል። በተያዘው በጀት ዓመት የወባ ሥርጭት እና መከላከል ሥራው ምን እንደሚመስል ነዋሪዎችን እና ባለሙያዎችን አነጋግረናል። በሽምብጥ ጤና ጣቢያ ያገኘናቸው አቻምየለው ይርጋ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በወባ ተጠቅተው ለወጭ መደረጋቸውን ነግረውናል። አሁንም በአካባቢው በርከት ያሉ ሰዎች በወባ መጠቃታቸው ገልጸዋል። የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ አማራጭ መፍትሄ ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ በሽምብጥ ጤና ጣቢያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ተጠሪ ባለሙያ ላኩብሽ ጥላሁን እንዳሉት ባለፈው በጀት ዓመት የወባ ሥርጭትን ለመከላከል ማኅበሰቡን በማሳተፍ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ተሠርቷል። በዚህ በጀት ዓመትም ዋነኛ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል። ከዚህ በፊት የተሰራጨውን አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀሙ በጤና ተቁሙ እና በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችም የቤት ለቤት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ ነው። የቀረበውን ውስን አጎበርም ለነፍሰ ጡር እና ለሚያጠቡ እናቶች ቅድሚያ እንዲያገኙ ተደርጓል። ይሁን እንጅ አሁንም የአጎበር እጥረት መኖሩን ገልጸዋል።
የወባ መድኃኒቶችን በጤና ተቋሙ በማሟላት በወባ ለተጠቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕክምና እየተሠጠ መኾኑን ገልጸዋል። ከሐምሌ/2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን በጤና ጣቢያው ለ1 ሺህ 926 ሰዎች ሕክምና ተሰጥቷል። ከዚህ በኋላ ያሉት ወራት የወባ መራቢያ ወቅት በመኾናቸው ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል። የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ባለፈው በጀት ዓመት በሽታውን “የአርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይገታሉ” በሚል መልዕክት የወባ መራቢያ ቦታዎች የቁጥጥር ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሕክምና የተሰጠ ሲኾን በሽታው ከዚህም በላይ እንዳይሠራጭ ተደርጓል ብለዋል።
አሁንም በክልሉ 40 ወረዳዎች 68 በመቶ የክልሉን የወባ ስርጭት እንደሚይዙ ገልጸዋል። ሥርጭቱን ለመከላከል በ18 ወረዳዎች 530 ሺህ 282 ቤቶችን የወባ ኬሚካል ለመርጨት ታቅዶ እስከ አሁን 80 በመቶ የሚኾኑትን ማሳካት ተችሏል ነው የተባለው። ለ26 ወረዳዎች ከተመደበው ግማሽ ሚሊዮን አጎበር በ20ዎቹ ወረዳዎች እየተሠራጨ ይገኛል። ቀሪ የአጎበር ሥርጭት እና የኬሚካል ርጭቱን እስከ መስከረም መጨረሻ ለማጠናቀቅም እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። ይሁን እንጅ አሁንም ግን የአጎበር እና የኬሚካል እጥረት መኖሩን ነው የገለጹት።
በተሠራው ሥራ በአብዛኛው ወረዳዎች የወባ ሥርጭቱ መቀነሱንም ገልጸዋል። በ2017 በጀት ዓመት በአንድ ሳምንት ብቻ እስከ 83 ሺህ የወባ ሕሙማን ሪፖርት መደረጉን ገልጸው በ2018 በጀት ዓመት ከሐምሌ ጀምሮ እስከ መስከረም 11/2018 ዓ.ም የወባ ሕክምና ያገኙት ሕሙማን 279 ሺህ 477 መኾናቸውን በማሳያነት አንስተዋል። አሁንም ግን 18 በመቶ የሚኾኑ ወረዳዎች የወባ ስርጭት መቀነስ አለማሳየታቸውን ጠቅሰዋል። በሽታው ጉዳት እንዳያደርስ ማኅበረሰቡ እና ሌሎች ተቋማት ከጤናው ተቋማት ጋር በመቀናጀት የአካባቢ ቁጥጥር ሠራው ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
ማኅበረሰቡም የወባ ምልክቶች ሲከሰቱ ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ሕክምናውን እንዲያገኙ አሳስበዋል። የጤና ባለሙያዎች ደግሞ ወባ የተገኘባቸውን ሰዎች በፍጥነት እና በወቅቱ እንዲያክሙም ጠይቀዋል። የወባ በሽታን ለማከም የሚያገለግሉ ግብዓቶች በከፍተኛ ወጭ የሚገቡ በመኾናቸው በትክክል ለተጠቃሚዎች የማድረስ ኀላፊነትን መወጣት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ከመስቀሉ ይቅርታን እንማራለን”ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ
Next articleየጸጥታ መዋቅሩ ውጤታማ ተግባራትን እንዲያከናውን የሕዝብ ድጋፍ ያስፈልገዋል።