
ጎንደር፡ መስከረም 16 /2018ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የ2018 ዓ.ም የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአማኞቹ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“በመስቀሉ ይቅርታ ይሰበካል ከመስቀሉ ይቅርታን እንማራለን” ያሉት ብፁዕነታቸው ክርስቶስን መስበክ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስን በመከራ መምሰል ነው ብለዋል። ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ እርግማንን ስለሻረበት መስቀል ዓለም አቀፍ እርቅ እና የሰላም ምልክት ኾኗል ብለዋል ብፁዕነታቸው። “ከኢየሱስ ክርስቶስ እንደተማርነው ይቅር በማለት የክርስቶስን አስተምሮ ልንመስል እና የይቅርታን መንገድ ልንከተል ይገባል” ነው ያሉት። ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ያሳየው ይቅርታ ስፍር ቁጥር እንደሌለውም አንስተዋል። አይሁድ የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከ300 ዓመታት በላይ ቀብረው ማቆየታቸውን አንስተው የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በንግስት ኢሌኒ አማካኝነት መውጣቱን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የሰላም እጦት ብዙ ፈተናን እንዳስከተለም ጠቅሰዋል። ፍቅር እና አንድነትን በማስቀደም ብሎም በማጽናት ከችግሩ መውጣት እንደሚገባም አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በጦርነት እና በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ ወገኖችን መደገፍ ያስፈልጋልም ብለዋል። ፍቅር እና አንድነትን በማስቀደም ቸርነት እና ይቅር ባይነትን በመላበስ በተግባር ክርስቶስን መከተል እንደሚገባም ጠቁመዋል። ዘመኑ ጸብ የጠፋበት፤ ሰላም እና ፍቅር የጸናበት፤ በምድሪቱ የሰው ደም የማይፈስበት የተቀደሰ ዘመን እንዲኾንም ተመኝተዋል።በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ለሚገኙ አማኞች ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!