
ባሕርዳር፡ መስከረም 16 /2018ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል አንደኛው ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የደብረ ሮሓ ቅዱስ ላሊበላ የአራቱ ጉባኤያተ መጻሕፍት ምሥክር መምህር ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አሥናቀ መስቀል እግዚአብሔር ፍጥረታቱን ይልቁንም የሰውን ልጅ ምን ያህል እንደሚወደው የገለጠበት የፍቅር ደብዳቤ ነው ብለውናል።

ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አሥናቀ ብዙዎች ነገረ መስቀሉ እለተ መድኃኒት፣ እለተ ፍሥሓ በሆነችው በእለተ ዓርብ የተጀመረ ይመስላቸዋል፤ ነገር ግን እለተ ዓርብ ነገረ መስቀሉ በግልጥ የተሰበከባት እለት ናት እንጂ ለነገረ መስቀሉ መነሻ እንዳልኾነች መጻሕፍት ያስረዳሉ ነው ያሉን።
ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በጥንተ ፍጥረት መላዕክት ዲያብሎስን ድል የነሱት በመስቀል ምልክት እንደኾነ ያስረዳሉም ብለዋል። ይህ ምልክት እንዴት ያለ ምልክት ነው ስንል ነቢዩ ኢሳያስ በትንቢቱ ላይ በዓርአያ ትዕምርተ መስቀል ሱራፌል ክንፋቸውን የሚዘረጉት በመስቀል ምልክት ነው ብሎ በሰማይ በመላዕክት አምልኮ ውስጥ መስቀል እንዳለ ገልጦልናል ብለዋል።
ሰውም በጥንተ ፍጥረት ሲፈጠር መልኩ የመስቀል ምልክት የታተመበት መኾኑን ነግረውናል። ይህንም ቅዱስ ያሬድ ሲያስረዳ ‘እግዚአብሔር ለምን በአንድ ግንባር ሁለት ዐይን፣ በአንድ ደረት ሁለት እጅ ፈጠረ ? ብሎ ከጠየቀ በኋላ ለምሥጢረ ሥላሴ ያለውን ምሳሌነት ገልጸዋል፤ ሁለተኛ ምሳሌነቱ ግን የመስቀል ምልክትን ለመግለጥ እንደኾነ አስረድቷል’ ብለውናል።
መስቀል በአባቶቻችን ዘመን በምሳሌ ተገልጧል ያሉት ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አሥናቀ “አብርሃምም ዐይኑን አነሣ፣ በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፣ አብርሃምም ሄደ፣ በጉንም ወሰደው፣ በልጁም ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው” ይላል ብለዋል።
ይህን ምሥጢር ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሲገልጥም ቀንዶቹ በእጸ ሳቤቅ የተያዙ በግን ተመልከቱ ፣ እጸ ሳቤቅም ማለት የመዳን እጽ መስቀል ነው በማለት ነው ያብራሩት በሚል ጠቅሰዋል። ሊቁ እንዲህ ማለቱ ይስሓቅ ከሞት የዳነበት በግ በእጹ ተስቦ የመጣ እንደኾነ አዳምም ከሞት የዳነበት ክርሥቶስ በመስቀል ላይ መሰቀሉን ሲገልጥ መኾኑን ነግረውናል።
ዳግመኛም አባቶቻችን በሥራቸው ሁሉ ይገልጡት ነበር ነው የሚሉት። “እስራኤልም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረው፣ እርሱም ታናሽ ነበረ፣ ግራውንም በምናሴ ራስ ላይ አኖረ፣ እጆቹንም አስተላለፈ” ይላልና አስተላለፈ ማለት አመሳቀለ ማለት ነው፤ መስቀል ከስቅለት አስቀድሞ በምሥጢር እዲህ ይታወቅ ነበር ብለዋል። በጌታ መሰቀል ጊዜ ዕለተ ዓርብ ደግሞ እግዚአብሔር ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ሕይወት የኾነውን ሞቱን በዕለተ ዓርብ የተቀበለው በመስቀል መኾኑን ነግረውናል። ሞቱ በመስቀል እንዲኾንለት የመረጠው በምክንያት መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ምክንያቶቹም በእጸ በለስ ምክንያት የመጣውን ሞት በእጸ መስቀል ድል ለመንሣት እና ሔዋን በለሷን ስትቆርጣት ደሟ ሲንጠፈጠፍ እጾች ሁሉ አብረው ቆስለው ስለነበር የመቁሰል ብድራቸውን በደሙ እና በቁስሉ ለመካስ ነው ብለዋል። ሁለተኛው ምክንያት እግዚአብሔር እና ፍጥረታት፣ ሰውና መላዕክት፣ ሰማይ እና ምድር ተለያይተው ነበርና ለማስታረቅ፤ ሁሉንም አንድ ለማድረግ መኾኑን ነግረውናል። ሊቁ ያዕቆብ ዘሥሩግ መስቀል በዕለተ ዓርብ እንዴት እንደከበረ ሲያደንቅ እግዚአብሔር በድንግል ማኅጸን ለራሱ ሁለት ክንዶችን ለምን ፈጠረ ?ሁለት ትክሻዎችንስ ለምን አዘጋጀ ? ብሎ ይጠይቅ እና ሲመልስ ሁለቱን ትክሻዎቹን መስቀልን ይሸከምባቸው ዘንድ እና ሁለቱንም ክንዶቹን መስቀልን ያቅፍባቸው ዘንድ ነው ብሎ ያደንቃል ይህም ሌላው ምክንያት ነው ይላሉ።
ይህ ሙዳየ ድኅነት መስቀል ከዕለተ አርብ በኋላ በደመ ክርሥቶስ የተቀደሰ ነውና ሙታንን እያሥነሳ ድውያንን እየፈወሰ የክርሥቶስን አምላክነት ይሰብክ ስለነበር አምላካቸውን በሰቀሉ አይሁዶች ለብዙ ዘመን ተቀብሮ ከቆየ በኋላ በንግሥት ኢሌኒ አማካኝነት መጋቢት አሥር ቀን ከተቀበረበት ወጥቷል ነው ያሉን። መስቀሉን ለማውጣት ቁፋሮ የተጀመረው መስከረም 17 ቀን ስለኾነ አሁንም ድረስ በዚህ ቀን በዓለ መስቀልን እናከብራለን ብለዋል።

ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አሥናቀ መስቀልን በ1446 ዓ.ም አጼ ዳዊት ከግብጽ እንደተቀበሉት ነግረውናል። ወደ ምድረ ኢትዮጵያ ያስገቡት ግን ልጃቸው አጼ ዘርዓያዕቆብ ናቸው። ቅዱስ መስቀሉ ከመጣ በኋላም ጌታ በቅዱስ ቃሉ እንዳለው በግሸን ደብረ ከርቤ መስቀለኛ ቦታ ላይ መቀመጡን ጠቅሰዋል። መስቀል በኢትዮጵያ የተገለጠው በመላዕክት ወይም በሰው አይደለም፤ የተሰበከውም በራሱ ዓለምን በፈጠረ በእግዚአብሔር ነው ነው ያሉን። ኢትዮጵያ ከዓለማት ሁሉ አስቀድማ መስቀልን ያወቀችው በጥንተ ፍጥረት ነው፤ ለዚህም ማሳያው ምስክሩ መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ በመስቀለኛይቱ ግሼን ደብረ ከርቤ አኑር የሚለው ልዩ ቃል መኾኑንም አንስተዋል።
መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበት ምክንያት በጊዜው ግብጽን ይገዛ የነበረው ንጉሥ ፈርኦን ክርስቲያኖች ላይ መከራ ያጸና ነበር፤ የግብጽ 47ኛ ፖትርያርክ አባ ሚካኤልን ጭምር አስሮ ነበርና ግብጻውያን ክርስቲያን አማኞች ለንጉሥ አጼ ዳዊት ጳጳሳቸውን እንዲያስፈታላቸው እና እነሱንም ነጻ እንዲያወጣቸው መልዕክት ልከው ነበር ብለዋል።
አጼ ዳዊትም ይህንን መልዕክት ሰምተው ለማስፈታት ሠራዊት አዝምተው በመሄድ ለይ እያሉ ካርቱም ሲደርሱ ጦር ከማዘምት ለምን ዓባይን አልገድብም ብለው አሰቡ ነው ያሉን። ከዛም አጼ ዳዊት ዓባይን ሊገድቡ እንደኾነ የግብጹ መሪ ሲሰማ ጳጳሱን ፈታ፤ ወርቅ እና ብር አስይዞ መማለጃ ላከ፤ ንጉሥ አጼ ዳዊት ግን በጊዜው ወርቅ እና ብሩን በመንበራቸው ኢትዮጵያ ላይ ስላላጡት ኢትዮጵያ በርሀብ፣ በቸነፈር፣ በተዛማጅ በሽታዎች ሁሉ እንዳትጎዳ ስለሚፈልጉ ይሄን የሚጠብቅላቸው እና ሀገራቸውን የሚያጸናላቸውን እጸ መስቀሉን ጠየቁ፤ የግብጹ መሪም መክረው መስቀሉን ወደ ኢትዮጵያ ላኩላቸው ብለዋል።
አብረው የመጡ ንዋየ ቅዱሳትም ሉቃስ የሳላት የጌታ እናት የማርያም ምስለ ሰዕል፣ አምስቱ ቅንዋት፣ ጌታ የተገረፈበት ጅራፋ፣ መግነዙ እና ሌሎችም የቅዱሳን አጽም እንደኾኑ ይነገራል ብለዋል። ንጉሡ በዛን ጊዜ ከዘመቱ በኋላ መስቀሉን የፈለጉበት ትልቅ ቁምነገር ሀገራቸውን ሰላም እንዲያደርግላቸው፣ ሕዝቡን እንዲያስማማላቸው፣ ከሕመም፣ ከደዌ እና ከችግር እንዲጠብቅላቸው ፈልገው መኾኑንም ተናግረዋል።

ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አሥናቀ ነገረ መስቀል የመዳን የርህራሄ የፍቅር እና የአንድነት ምልክት መኾኑን ገልጸዋል። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በመስቀሉ ሰላምን አደረገ” ያለው ለዚህ ነው፤ የክርስቶስ መስቀል የዘላለማዊ ሰላም ምልክት ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን መልዕክቱ ላይ “እርሱ ሰላማችን ነውና” በማለት ያብራራልን ክርስቶስ በመስቀል ስለእኛ የከፈለውን ዋጋ ሲገልጥ ነው ብለዋል።
ስለዚህ በመስቀል ላይ የሚታዩ ትምህርቶች ግልጽ እና ጎላ ብለው የተጻፉ ናቸው፣ እነርሱም ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት ናቸው ነው ያሉት። ” ሳንከፋፈል በመስቀል የተገኘውን ሰላም ልንጠብቅ እና በመካከላችን ልናሰፍንም ይገባል” ብለዋል። ወደ ግራ የበደሉንን ይቅር ልንል፣ ወደ ቀኝም ወንድሞቻችንን ልናስብ ይገባል፤ ጌታችንም “የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ፣ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ ይቅር ይላችኋል” እንዳለን ንጹሕ ባሕርይ እርሱ የበደልነውን ይቅር ይለን ዘንድ እኛም ይቅርታን ገንዘብ ማድረግ እንደሚገባን አስተምሮናል ነው ያሉት። ሀገራችን ኢትዮጵያ መስቀሉን እንደተሸከመች ሁሉ እኛም እንደ ሕዝብ የክርስቶስ መስቀል ፍሬዎች የኾኑትን ፍቅርን፣ አንድነትን እና ሰላምን ገንዘብ በማድረግ የመስቀሉን በዓል ማክበር ይገባናል ብለዋል።
ዘጋቢ ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!