
ባሕር ዳር፡ መስከረም 15/2018 ዓ.ም ( አሚኮ) ነገረ መስቀሉን ስናስብ ታሪኩ የሚመዘዘው ኢየሱስ ወደ ዚህ ዓለም መጥቶ አዳምን ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ከገባለት ቃል እንደኾነ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መምህር ይትባረክ ደምለው ይገልጻሉ።
ለአዳም የገባለት ቃል ኪዳን ይፈጸም ዘንድ ኢየሱስ በዚህ ዓለም 33 ዓመት ከሦስት ወር ከቆየ በኋላ በኢየሩሳሌም በሚገኝ ቀራንዮ በተባለ አደባባይ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የገባለትን ቃል ኪዳን ፈጽሞ ከወደቀበት የሲኦል ቦታ አውጥቶታል። መምህር ይትባረክ መስቀል ሲነሳ ኢየሱስ እስከተሰቀለበት ጊዜ ድረስ የወንጀለኞች እና ክፉ የሠሩ ሰዎች መቅጫ ኾኖ በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ያገለግል ነበር ብለዋል። የመስቀሉ የወንጀለኛ መቅጫነት አብቅቶ ጊዜው ሲደርስ መስቀሉ ይከብር፣ አዳምም ከአባቱ ይገናኝ ዘንድ ኢየሱስ በቀራኒዮ አደባባይ በሁለት ወንበዴዎች መካከል ተሰቅሏል። ይህም ጥልን ገሎ የሰውን ልጅ ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቋል ይላሉ።
የመስቀሉ ነገር ያልገባቸው አይሁዳውያንም ገለውት አልበቃ ሲላቸው እና በአካለ ስጋ ከእነሱ ጋር ሳለ የሚሠራው ታምራት ይረብሻቸው ስለነበር ከሞተ በኋላም የሰቀሉበት መስቀል ታምራት እየሠራ እረፍት አልሰጣቸውም። ቅናታቸው ቅጥ ሲያጣ መስቀሉ እንዳይለይ ሁለቱ ወንበዴዎች ከተሰቀሉበት መስቀል ጋር በማድረግ ሦሥት ጉድጓድ ለየብቻ ቆፍረው ጎሎጎታ ተብሎ በሚጠራ ቦታ በመቅበር አዋጅ አስነገሩ ይላሉ መምህር ይትባረክ። አዋጁም ማንኛውም ሰው በዚያ ቦታ ቆሻሻ እንዲደፋ የሚያዝ ነበር፤ ሰዎችም አዋጁን አክብረው ለ300 ዓመታት በጎልጎታ ላይ ሦሥት ተራራዎች እስኪፈጠሩ ድረስ ቆሻሻ ሲደፉበት ኑረዋል። ይህ የአይሁድ ሴራ የድኅነት መስቀሉን ለመሰወር የፈጠሩት ሴራ ነበር ሲሉም አስረድተዋል።
አይሁድ መስቀሉን ለመሠወር ጥረት አድርገው የተሳካላቸው ቢመሥልም መስቀሉን ግን ከክርስቲያኖች አእምሮ ግን መሰወር አልቻሉም። መስቀሉ በዓለም ላይ ባሉ ክርስቲያኖች ልብ ውስጥ የታተመው የድኅነት መስቀል ፈላጊዎቹ ብዙም ነበሩ ይላሉ። ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል ንግሥት ኢሌኒ ትገኝበታለች፤ ንግሥት ኢሌኒ ትኖር የነበረው በምሥራቅ አውሮፓ ቆስጠንጥኒያ ተብሎ በሚጠራ ከተማ ውስጥም ነበር፤ ይህ ስፍራ ዛሬ የቱርኪየ ዋና ከተማ ኢስታንቡል ኾኖ በማገልገል ላይም ይገኛል ብለዋል።ንግሥት ኢሌኒ ልጇ ቆስጠንጢኖስ ንጉሥ እንደሚኾን ይጠበቅ ነበር እና ልጇ ተጠምቆ ክርስትናን ከተቀበለ መስቀሉን ፈልጋ እንደምታገኝ ተስላ ስለነበር ልጇ እንደተሳለችው የሮም ቄሳር ገዥ ኾኖ በ327 ዓ.ም ሲሾም እና ክርስትናን ሲቀበል ይህን ምኞቷን ለማሳካት ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛለች፤ መስቀሉን ፍለጋ ይላሉ መምህር ይትባረክ።
ንግሥት ኢሌኒ ስፍራው ላይ ስትደርስ መስቀሉ ይገኝበታል የተባለውን ቦታ የሚያሳይ አይሁዳዊ ማግኘት አልቻለችም፤ ከብዙ ጥረት በኋላ ግን አንድ በዕድሜው የገፋ ኪራኮስ የተባለ ሰው መስቀሉ ከሦሥቱ ተራሮች ውስጥ በአንዱ እንደኾነ እና ለይቶ ግን እንደማያውቀው ይነግራታል።
እሷም ምን ማድረግ እና መለየት እንደምትችል ስትጠይቀው አረጋዊው ኪራኮስ ብልህ ነበርና ደመራ ደምራ እጣን ጨምራ ጸሎት በማድረስ ምልክት እንደምታገኝ ይነግራታል። እሷም እንደተባለችው መስከረም 16 ደመራ ደምራ እጣን ጨምራ ብታቃጥለው ጭሱ ወደ ሰማይ ወጥቶ መስቀሉ ወደ ሚገኝበት ተራራ ሰግዷል።
በዚህም ንግሥት ኢሌኒ የመስቀሉን ፍለጋ ቁፋሮ መስከረም 17 አስጀምረዋለች። ከሰባት ወራት ቁፋሮ በኋላም መጋቢት 10 ቀን መስቀሉ ተገኝቷል። መስቀሉ ሲገኝም ከሌሎቹ አብረው ከተቀበሩት በተለየ የሚያበራ ነበር። ባወጡትም ጊዜ አካባቢው በብርሃን ተሞልቷል፤ ከሁለቱ በተለየም ልዩ ልዩ ታምራትን አድርጓል። በዚህ ጊዜም ሰዎች ይኸዋ ይኸዋ ብለዋል። ይህም ዛሬ ክርስቲያኖች እዮሃ እያሉ ደመራውን ዞረው የሚለኩሱትም ከዛ የመጣ ለመኾኑ ማሳያ እንደኾነም ጠቁመዋል።
በደመራው የሚበራው ችቦም ንግሥቲቱ ሀሳቧ ሲሳካ እና መሥቀሉን ስታገኝ ደስታዋን ለመግለጽ ችቦ ልካለታለች። ችቦውም ከተራራ ተራራ እየተቀባበሉ ከንጉሥ ቆስጠንጢኖስ አድርሰውታል። እሱም ተቀብሎ ደስታውን ከእናቱ ጋር እንጎረጎባሽ ብሎ ተካፍሏል ይላሉ።
ይህም እንኳን ደሳለሽ መስቀሉን ለማግኘት በቃሽ የሚለውን ደስታ ለመግለጽ ሲኾን ኢትዮጵያውያን አሁን ላይም ይህን ቃል በስፋት እንደሚጠቀሙት ነው ያስረዱት። ከደስታው በኋላ ወደ ስፍራው ያመራው ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በአካባቢው ቅዳሴ ቤት አሠርቶ መስከረም 17 ቁፋሮው በተጀመረበት ዕለት የመስቀሉን ታቦት አክብረው አስገብተው ሁለት ጊዜ ደስታ እንዳደረጉ ነው ያብራሩት።
ደመራ ሲከበር አንዳንድ አካባቢዎች በ16 ማታ ደምረው ሲያቃጥሉ አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በ17 ጠዋት ሥርዓቱን ያከናውናሉ። ይህም ልዩነት ሳይኾን ሥርዓቱን በአንድ ላይ ለመፈጸም ካለ ፍላጎት የሚመጣ እንጅ ትክክለኛው ደመራው በ16 በዋዜማው ተደምሮ ከተቃጠለ በኋላ በ17 ደግሞ የመስቀሉ ፍለጋ ቁፋሮ የተጀመረበት በዓል እና ቅዳሴ ቤቱ የተፈጸመበት በዓል እንደሚከበር ነው መምህሩ ያስረዱን።
መልካም የደመራ በዓል ተመኘን!
ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!