በብሔረሰብ አሥተዳደሩ 180 ተማሪዎች ከ300 በላይ ውጤት አስመዝግበዋል።

13
ሰቆጣ: መስከረም 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር 180 ተማሪዎች የሀገር አቀፍ ፈተናውን ከ300 በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።
ተማሪ ፍቅርተ እሸቱ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ ውጤት ካመጡ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ቀዳሚዋ ናት። 524 ነጥብ 99 በማምጣት ለዩኒቨርስቲ የሚያበቃ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጻልናለች። ውጤታማ የመኾኗ ምስጢር በርትታ ማጥናቷ እና የመምህራኑ ድጋፍ መኾኑንም ነግራናለች። ሴትነቷ ከውጤታማነት እንዳልመለሳት የምትናገረው ተማሪዋ በፈተና ወቅት የነበረው የጸጥታ ችግር እና የመፈተኛ ቦታው መራቅ በውጤቷ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደነበረው አስታውሳለች።
የቤተሰብ ድጋፍ እና ክትትል ለልጆች ውጤታማነት አይነተኛ ሚና እንዳለው የተናገሩት ደግሞ የፍቅርተ ወላጅ እናት ወይዘሮ አበሩ ካሳዬ ናቸው። የሥራ ጫና እንዳይኖርባት ከማድረግ ጀምሮ ለጥናት የሚረዱ አጋዥ መጽሐፍት በመግዛት እና አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት ሲያግዟት እንደነበር ተናግረዋል። በቀጣይም ካለመችው ደረጃ እንዲትደርስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ወይዘሮ አበሩ ገልጸዋል።
የዋግ ስዩም አድማሱ ወሰን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ500 በላይ ተማሪዎች አስፈትኗል። 48 ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት ማስመዝገባቸውን የገለጹት ደግሞ የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ግርማ መክብብ ናቸው። በቀጣይ የሚያልፉ ተማሪዎችን ቁጥር ለመጨመር በትኩረት እንደሚሠሩ ነው ርእሰ መምህሩ የገለጹት።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከ3 ሺህ 900 በላይ ተማሪዎች የሀገር አቀፍ ፈተና ወስደዋል። 180 ተማሪዎች የ300 በላይ ነጥብ ማምጣታቸውን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ፍታለሽ ምህረቴ ገልጸዋል።
ሦስት ተማሪዎች ከ500 በላይ አምጥተዋል ያሉት ምክትል ኀላፊዋ 4 ነጥብ 5 በመቶ የማለፍ ምጣኔ በዞኑ አንደተመዘገበ ጠቁመዋል።
በተያዘው ዓመት የተማሪዎችን የማለፍ መጠን ከፍ ለማድረግ ከተማሪ ምዝገባ ጀምሮ በአደረጃጀት እየሠሩ መኾኑን ነው ምክትል ኀላፊዋ የገለጹት
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየመስቀል በዓል እና የፊፊ ባሕላዊ ጨዋታ- በጃዊ
Next articleከቱርክ እስከ ጎልጎታ መስቀሉን ፍለጋ።