የመስቀል በዓል ለማኅበረሰቡ አብሮነት እና የእሴት ግንባታ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው።

2
ባሕርዳር፡ መስከረም 16 /2018ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕል እና ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ተመስገን በየነ (ዶ.ር) የመስቀል በዓል ለማኅበረሰቡ አብሮነት፣ እሴት እና አንድነት ትልቅ ፋይዳ አለው።
ዶክተር ተመስገን የመስቀል በዓል ኢኮኖሚውን ከመደጎም ባለፈ ለማኅበራዊ ሕይዎት መጎልበት ያለው ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አለመኾኑን ነው ያስገነዘቡት። የመስቀል በዓል ቤተሰቦች፣ ጉረቤቶች እና መላው ማኅበረሰብ የሚሠበሠብበት፣ አብሮ የሚበላበት፣ የሚጠጣበት፣ ደስታውን የሚገልጽበት እና ግንኙነቱን የሚያጠናክርበት እንደኾነም ገልጸዋል። ይህ በዓል ሰዎች ባሕላዊ እሴቶቻቸውን እና ማንነታቸውን የሚገልጹበት ነው ያሉት ዶክተር ተመስገን ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ባሕል እና ታሪክ ሀገር መኾኗ የሚታይበት ሁነት እንደኾነም ጠቁመዋል።
መምህሩ የመስቀል በዓል በ2013 በዩኔስኮ በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ዉስጥ መካተቱን ገልጸዋል። ይህም ከኢትዮጵያውያን ባለፈ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ያለው በዓል እንዳደረገውም ነው ያብራሩት። የመስቀል በዓል ለንግዱ ማኅበረሰብ እና ለአገልግሉት ሰጭ ተቆማት የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ዕድል መፍጠር የቻለ በዓል እንደኾነም አስገንዝበዋል። የመስቀል በዓል የሃይማኖቱ ተከታዮችን በጋራ፣ በአንድነት እና በፍቅር እንዲኖሩ የሚያስችል እንደኾነም አብራርተዋል። በአማኞች መካከልም ጠንካራ አማኝ እንዲፈጠር እና የሃይማኖቱ ዕሴቶች እንዲጠናከሩ እየተጫዎተ ያለው ሚና ከፍ ያለ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት።
ዘጋቢ ፦ ሰመሀል ፍስሀ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በተለያዩ ዘርፎች ላይ አጠቃላይ ውይይት አካሂደናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየክልሉን ሰላም አስተማማኝ በማድረግ ማኅበረሰቡ በሙሉ አቅሙ ወደ ልማት ሥራዎች እንዲዞር ማድረግ ይገባል።