በመስቀሉ ይቅር እንደተባልን እኛም እንዲሁ ይቅር እንባባል።

6
ባሕር ዳር፡ መስከረም 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መስቀል ሰቀለ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲኾን ጥሬ ፍቹ መስቀል ማለት መስቀያ፣ ማንጠላጠያ ማለት ነው፡፡
ሚስጥራዊ ትርጉሙ ግን መስቀል ማለት መከራ፣ የክርሲቲያኖች አርማ፣ የአጋንንት መቅጫ፣ የክርስቶስን ፍጹም ፍቅሩን ማየት የተቻለበት ማጉያ መነጽር ማለት እንደኾነ የትርጓሜ መጽሐፍት መምህር እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የገዳመ ዮርዳኖስ ትምህርት ቤት የመለኮት ስብከተ ወንጌል ኀላፊ መምህር ዘላለም በላይ ይገልጻሉ። የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ዳራው ወይም ደግሞ ሃይማኖታዊ አስተምህሮው ሲገለጽ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠላትን ድል ያደረገበት፣ ሞትን ያጠፋበት፣ አለመግባባትን ያስወገድንበት ነው፡፡
ይህንን በመገንዘብም ከጥንት ጀምሮ መስቀልን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በዓል አድርጋ ታከብረዋለች፡፡ መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ጠፍተው እንዳይቀሩ ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን ለመፈጸም ከ5 ሺህ 500 ዘመን ቆይታ በኋላ ዕለቱን፣ ሰዓቱን፣ ደቂቃውን ሳያሳልፍ በፍጥረታቱ እጅ ተይዞ ወደ መስቀል ወጥቶ ደመ መለኮቱ በመስቀሉ ከነጠበበት፣ ስጋው በመስቀሉ ካረፈበት በኋላ መስቀሉ ኀይለ እግዝብሔር ተሰጥቶት አጋንንትን ሲያወጣ፣ ለምጻሞችን ሲያነጻ፣ ሙታንን ሲያስነሳ፣ እውራንን ሲያበራ አይሁዶች ሲያዩ ታሪኩ እንዲጠፋ፣ ከምድረ ገጽ እንዳይገኝ በመምከር የኢየሩሳሌም ሕዝብን በመሠብሠብ መሬት ቆፍረው በመቅበር ሕዝቡ በሙሉ የቤቱን ቆሻሻ እያወጣ እንዲከምርበት አደረጉ፡፡
ይህ በኾነ ከ300 ዓመት በኋላ የሮም ሀገር ንጉስ ቆንጠንጢኖስ እናት ንግስት ኢሌኒ የምትባል ሴት መስቀሉን ፈልጊ ቅዱሳን መካናትንም አሰሪ የሚል ራዕይ ይታያት እና ትእዛዙን ለመፈጸም ወደ እየሩሳሌም አቅንታለች፡፡ እየሩሳሌም ደርሳ አይሁድን በመሠብሠብ የጌታየን መስቀል እሻለሁ ፈልጉልኝ የት አደረሳችሁት በማለት ጠየቀቻቸው፡፡ አይሁዶች የመስቀሉን መውጣት አልፈለጉምና “መስቀል አልቀበርንም ሰውም አልሰቀልንም” በማለት ተከራከሩ፡፡ ንግስት ኢሌኒም የመስቀሉ ፍቅር አድሮባታልና በመንፈስ ቅዱስ ጸንታ ፍለጋዋን ቀጠለች፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ሠብሥባ ስትጠይቅ አይሁድም በሀገሪቱ ያሉ ሁለት አረጋውያን አሉና እነሱን ጠይቂ አሏት፡፡ ንግስት ኢሌኒም አረጋውያኑን በማስመጣት ለሦሥተኛ ጊዜ ጠየቀች አረጋውያኑም የት እንደተቀበረ እንደማያውቁ ነገሯት፡፡
ንግስት ኢሌኒ በአይሁዶች ምላሽ ተስፋ ሳትቆርጥ ወደ ጎልጎታ በመሄድ ድንኳን አስጥላ 40 ቀን ከምግብ በመከልከል እያነባች የመስቀሉ ቦታ እንዲገለጽላት ወደ ፈጣሪዋ መጸለይ ጀመረች፡፡ ፈጣሪዋ ኢየሱስ ክርስቶስ የልቧን ቅንነት እና መሻት አይቶ በ40ኛው ቀን መላኩ ቅዱስ ገብርኤልን ላከላት፡፡ ቅዱስ ገብርኤል የመስቀሉን እጹብ ድንቅነት በመግለጽ የተቀበረበትን ቦታ አዛውንቶች ሊነግሯት እንደሚችሉ ነግሯት ተሰወረ፡፡ ንግስት ኢሌኒም ስለተደረገላት ነገር አምላኳን በማመስገን አዛውንቶችን በማስጠራት ጠየቀቻቸው፡፡ አዛውንቶቹም ከብዙ ማቅማማት በኋላ ቅድመ አያቶቻችን በዚህ አካባቢ እንደቀበሩት ሲያወሩ ሰምተናል ስለዚህ ደመራ ደምረሽ እጣን አጭሰሽ ጭሱ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች የሚያርፍበትን አካባቢ አስቆፍሪ በማለት ነገሯት፡፡
እርሷም ደመራ አስደምራ በኢየሩሳሌም ሊቀጳጳስ አባ መቃርስ ጸሎት አስጸልያ ስንድሮስ የሚባል እጣን በማጨስ ጭሱ ከመንበረ ስላሴ ደርሶ በመመለስ ወደ ምድር ሰገደ፡፡ የሰገደበት ቦታም የክርስቶስ መስቀል የተቀበረበት አካባቢ ነበር፡፡ ጭሱ ምልክት ሲያሳያት ንግስቲቱ በመደሰት መስከረም 17 ቀን ቁፋሮ አስጀመረች መጋቢት 10 ቀን በቀኝና በግራ አብረው ተሰቅለው ከነበሩት መስቀል በተለየ ከመስቀሉ ራስጌ ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሳዊ አይሁድ የሚል ጽሑፍ የተጻፈበት መስቀል አገኘች፡፡ በመስቀሉ ነጸብራቅ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች በድንጋጤ ወደቁ፡፡ ይልቁንም ከመጋቢት 10 እስከሚቀጥለው መስከረም 17 ድረስ ዓለም ብርሃን ኾነች፡፡ መጋቢት 10 የዐቢይ ጾም ስለሚውል በዐቢይ ጾም ሥርዓቱ ደስታ ፌሽታ ስለማይፈቅድ አባቶች የመጋቢት 10 በዓልን ወደ መስከረም 17 በማምጣት በዓሉ እንዲከበር ሥርዓት ሠሩ፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ክርሲቲያኖች መስከረም 17 ደመራ ተደምሮ እጣን ተጨምሮ አባቶች ምህላ አድርሰው ጸሎት ከጸለዩ በኋላ ሥርዓቱ ሲያልቅ ደመራውን በመለኮስ በዓሉ ይከበራል፡፡ ከደመራው የሚወጣው ጭስም የቅድስት ኢሌኒን ታሪክ ለመድገም እንደሚደረግ አስተምህሮው ያስረዳናል ይላሉ፡፡ በሌላ መልኩ መስቀል ማለት ሰው እና እግዚአብሔር፣ ሕዝብ እና አሕዛብ የታረቁበት፣ ጨለማ የተወገደበት፣ ብርሃን ያየንበት፣ በዓለም 5 ሺህ 500 ዘመን በአጋንት እግር እየተጠቀጠቁ የነበሩ የሰው ልጆች በሙሉ በመስቀሉ ዙፋን ላይ አድሮ ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅር ያላቸው፤ ወደ ሰላም ወደ እርቅ ወደ ሕይዎት እንዲመጡ የተደረገበት ትልቅ የሰላም መሳሪያም ነው ብለዋል፡፡
መስቀል እንደ ሀገር ሲገለጽ ደግሞ በመጀመሪያ መስቀል የቤተ ክርሲቲያኗ ሃብት፣ በሁለተኛ ደረጃ የሀገር ሃብት ነው፣ በሦሥተኛ ደረጃ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኒስኮ ተመዝግቦ የዓለም ሃብት ነው ይላሉ መምህር ዘላለም፡፡ ይህንን ተከትሎ በተለይ በዓሉ በሚከበርበት ወቅት ከሀገር ውስጥም ኾነ ከውጭ ሀገራት በሚመጡ ታዳሚዎች ሀገር እንደሀገር የምታገኘው የውስጥ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ያደርጋል ከዚህ ጋር ተያይዞ በዓለም ላይ ላሉ ሁሉ የሀገሪቱን የገጽታ ግንባታ ከፍ ለማድረግም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም ብለዋል፡፡
መምህር ዘላለም ለሁሉም ኦርቶዶክሳውያን ተዋህዶ ዓማኞች እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ በማለት የመስቀል በዓልን ሲከበር ሰላምን፣ ፍቅርን እና አንድነትን፣ ይቅርታን እያሰብን፣ እግዚአብሔር በመስቀሉ ተሰቅሎ የከፈለልንን የፍቅሩን ዋጋ እያሰብን ለሀገር አንድነት መተባበር፤ ይቅር መባባል እንዲኖር እና ሰላም እንዲሰፍን የመስቀሉን ውለታ ሳንረሳ ጥላቻን ለማስወገድ በመጸለይ እግዚአብሔርን መጠየቅ ይኖርብናል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“በመደመር ደመራ እየተመራን፣ በትጋት እየቆፈርን፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና እናወጣዋለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በተለያዩ ዘርፎች ላይ አጠቃላይ ውይይት አካሂደናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)