“የሰላምን ዋጋ ከመስቀሉ መማር ይገባል” ብጹዕ አቡነ ሚካኤል

4
ደብረታቦር፡ መስከረም 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል በዓል በአደባባይ ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ ነው። በዓለም የቅርስ መዝገብ (ዩኔስኮ) ከሰፈሩት የማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ የኾነው ይህ በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች መካከል የደብረታቦር ከተማ አንዷ ናት።
የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ሚካኤል አማኞች በዓሉን ለሀገር ሰላም ከልብ በመፀለይ እና በመተሳሰብ ማክበር እንደሚገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል። ሰላምን በመጠበቅ በዓሉን ካለፈው ዓመት በተሻለ ማክበር ይገባል ያሉት ብጹዕነታቸው የእርስ በእርስ ግጭቱን በሰላማዊ መንግድ መፍታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ሕጻናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲገቡ የሚደረገው ጥረት አበረታች መኾኑንም ጠቁመዋል።
መስቀል የጥል ግድግዳ የፈረሰበት፣ ሰላም የተሰበከበት ነው ያሉት ብጹዕ አቡነ ሚካኤል የሰላምን ዋጋ ከመስቀሉ መማር እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ለመስቀል እና ደመራ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል። የሰላም ምልክት የኾነው የመስቀል በዓል ሲከበር ሁሉም ሰው ሰላምን በመፈለግ ሊኾን ይገባል ያሉት ደግሞ ሃሳባቸውን ለአሚኮ የሰጡ በከተማዋ የሚኖሩ የሃይማኖቱ ተከታዮች ናቸው። በከተማዋ ያለውን አንጻራዊ ሰላም በማጽናት በዓሉን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየወባ በሽታ ስርጭትን ለመቀነስ ምን እየተሠራ ነው?
Next article“መስቀሉ በመስቀለኛ ስፍራ”