
ባሕር ዳር: መስከረም 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወባ በሽታ በወባ ትንኝ ንክሻ አማካኝነት የሚመጣ አደገኛ በሽታ ነው። በሽታው በተለይም በክረምት መግቢያ እና መውጫ ላይ ለትንኞች መራባት ምቹ ጊዜ በመኾኑ ሥርጭቱ ከፍተኛ ነው። በአማራ ክልል በከፍተኛ ሁኔታ የጤና ችግር ነው።
በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የወባ ህሙማን ቁጥር የተመዘገበ መኾኑን ከክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ለእነዚህ ህሙማን ህክምና ለመስጠት እና ለተያያዥ ወጭዎች በትንሹ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንደጠየቀም መረጃው ያሳያል። ይህ ደግሞ በማኅበረሰቡ እና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ መኾኑን የሚያሳይ ነው። በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አየሁ ጓጉሳ ወረዳ ነዋሪ የኾኑት ወይዘሮ ሙሉ አለነ ባለፈው ዓመት በርካታ ሰዎች በወባ በሽታ ታመው እንደነበር ትውስታቸውን ነግረውናል። የወባ በሽታን ለመከላከል የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀሙ፣ አካባቢያቸውን እንዲያጸዱ እና የበሽታ ምልክት ሲታይባቸው ቶሎ ወደ ሕክምና እንዲሄዱ በጤና ባለሙያዎች ምክር እንደተሰጣቸውም አንስተዋል።
እርሳቸው የተሰጣቸውን ምክር በአግባቡ በመተግበራቸው በቤተሰቦቻቸው ላይ የወባ በሽታ እንዳልተከሰተ ነው የገለጹልን። ይሁንና በአካባቢያቸው የባለሙያዎችን ምክር ባለመተግበራቸው በወባ በሽታ መጠቃታቸውን ተናግረዋል። የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ተከስቶ ታካሚዎች በግል እየገዙ እንደነበር አስተውሏቸውን ገልጸዋል። ወረርሽኙን ለመከላከል የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት ተካሂዷል ነው ያሉት። አጎበርን በተመለከተ ማኅበረሰቡ የነበረውን እንዲጠቀም እንጅ በአዲስ ሥርጭት አለመኖሩን ነው የተናገሩት። በየሳምንቱ አካባቢያቸውን በማጽዳት እና ውኃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስ ተግባር ተሠርቷል ነው ያሉት።
የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተመስገን ፈንታሁን ባለፈው በጀት ዓመት በወረዳው ከፍተኛ የኾነ የወባ ወረርሽኝ ተከስቶ እንደነበር አንስተዋል። በአካባቢው ከፍተኛ የኾነ ሙቀት መኖሩ አንዱ ምክንያት ቢኾንም የተከሰተው ወረርሽኝ ያልተጠበቀ እና በቂ ዝግጅት ያልተደረገበት እንደነበር ጠቁመዋል። በወረዳው ከ48ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍል በወባ በሽታ ተይዞ የሕክምና አገልግሎት መሰጠቱን ነው የተናገሩት፡፡ የተከሰተው ወረርሽኝ እንዳይቀጥል ኅብረተሰቡን በንቅናቄ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እንዲሠራ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ወባን ለመከላከል አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀም፣ አካባቢውን እንዲያጸዳ እና የህመም ስሜት ሲኖር በቶሎ እንዲታከም የምክር አገልግሎት ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡ በወረዳው በ11 ቀበሌዎች የጸረ ወባ ኬሚካል እርጭት እንደተካሄደም ነው የተናገሩት።
በጤና ተቋማት የሕክምና ቁሳቁስ ግብዓት ባለፈው እጥረት አጋጥሞ ስለነበር ለቀጣይ እንዳይከሰት በዚህ ዓመት ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው ኹኔታ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 25 በመቶ ሥርጭቱ መቀነሱን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የአካባቢ ቁጥጥር ሥራው እና የኬሚካል ርጭቱ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ቤት ለቤት በሚደረገው አሰሳ ኅብረተሰቡ የአጎበር አጠቃቀም ችግር መኖሩ ተስተውሏል ያሉት ኀላፊው ለሌላ አገልግሎት እንደሚያውሉትም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በክረምት መውጫ ላይ ወባ ሊከሰት ስለሚችል ቀድሞ ለመከላከል በየሳምንቱ የአካባቢ ጽዳት እና ቁጥጥር ሥራዎችን በወጣቶች ንቅናቄ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ወባን የመከላከል ሥራው እንዳለ ኾኖ ከተከሰተም ህክምናውን ለመስጠት በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ አየለ አልማው የብሔሰብ አሥተዳደሩ በክልሉ ወባ ከሚከሰትባቸው ዞኖች አንዱ ነው ብለዋል፡፡ በተለይም አየሁ ጓጉሳ፣ ቻግኒ፣ ዚገም፣ ጓንጓ እና ጃዊ ወረዳዎች በዞኑ 82 በመቶ የሚኾነው ወባ የሚከሰትባቸው ወረዳዎች መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
በክረምት መግቢያ እና መውጫ ወባ በሚከሰትባቸው ጊዜያት ባለፈው ዓመት ከፍተኛ የኾነ ሥርጭት ነበር፤ ከክልሉ በሁለተኛ ደረጃ ላይ መጠቀሱንም አንስተዋል፡፡ በዓመቱ 390 ሺህ 869 የወባ ህሙማን የተመዘገበ ሲኾን ሞት አጋጥሞ እንደነበርም አንስተዋል፡፡ ወረርሽኙን ተከትሎ ወባን ለመከላከል ወሳኝ የኾነው የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ላይ ማኅበረሰቡን በማነቃነቅ በመኾኑ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ፕሮግራም አሥተባባሪ ዳምጤ ላንክር ባለፈው ዓመት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የወባ በሽታ ወረርሽኝ ተከስቶ እንደነበር ተናግረዋል። በተለይሞ ደግሞ ደቡብ ጎንደር፣ አዊ ብሔረሰብ፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎጃም እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች ከፍተኛ የወባ ህሙማን ቁጥር የተመዘገበባቸው ናቸው ብለዋል።
በሽታውን ለመከላከል ከየወረዳዎች የሚመለከታቸው የጤና ባለሙያዎች ሥልጠና መሠጠቱን ተናግረዋል። የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ላይ በትኩረት እንደተሠራም ገልጸዋል። በተጨማሪም ከፍተኛ ስርጭት ባለባቸው ወረዳዎች የኬሚካል ርጭት እና መካከለኛ ሥርጭት ላለባቸው ወረዳዎች አጎበር መሠራጨቱንም ገልጸዋል። የወባ ሕክምና ግብዓትን በተመለከተ እጥረት አለመኖሩን ነው የተናገሩት። የወባ በሽታን ለመከላከል የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ውጤታማ፣ ወጭ ቆጣቢ እና ሁሉም ሰው ሊተገብረው የሚችል በመኾኑ ሁሉም ሰው አካባቢውን በማጽዳት እና የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታወችን በማፋሰስ ወባን መከላከል ይቻላል ነው ያሉት።
በተሠሩ ሥራዎች ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር አሁን ላይ መቀነሱን ተናግረዋል። ይሁን እንጅ አሁን ያለንበት የክረምት መውጫ ወቅት ለወባ መራባት ምቹ ጊዜ በመኾኑ ኅብረተሰቡ የመከላከል ሥራዎች ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ ወባ የክልላችን ዋናው የጤና ችግር ነው ያሉት አሥተባባሪው ኅብረተሰቡ በወባ በሽታ ምክንያት ለህክምና ወጭ እና በህመም ምክንያት ምርታማነትንም የሚቀንስ በመኾኑ ኅብረተሰቡ የመከላከል ሥራው ላይ ትኩረት እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!