
ፍኖተ ሰላም: መስከረም 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት የመስቀል በዓል በድምቀት እንዲከበር ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ከሚከበሩ የአደባባይ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የመስቀል በዓል አንዱ ነው።
የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ዘካርያስ “የመስቀል በዓል ጨለማው ተገፎ የብርሃን መገለጥ የሚታይበት ነው፤ በብርሃን ደግሞ ወደ ሰላም ልንሸጋገር ይገባል ብለዋል።
ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር ትህትናን በመላበስ መኾን እንዳለበት ገልጸዋል። በፍቅር እና በመከባበር እና እጅ ለእጅ ተያይዘን ስለሰላም በመዘመር ማክበር አለብን ነው ያሉት።
በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ክፍል ምክትል አዛዥ ምክትል ኮማንደር አዳምጣቸው ዓለሙ ናቸው።
በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከወጣቶች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም ገልጸዋል።
በዓሉ በሰላም እንዳይከበር ሊያሰጉ የሚችሉ ነገሮችን ቀድሞ በመለየት እና ለጸጥታ ኃይሉ ስምሪት በመስጠት ሰፊ ተግባር እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ደመራው ሲለኮስ የእሳት ቃጠሎ እና ሌሎች አደጋዎች እንዳይከሰቱ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች መከናወናቸውንም ነው የተናገሩት።
ኅብረተሰቡ በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!