
ደባርቅ: መስከረም 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወርልድ ቪዥን የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው በደባርቅ ወረዳ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ አድርጓል።
ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው በደባርቅ ወረዳ የሚገኙ 300 የሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው የዓይነት ድጋፍ የተደረገላቸው። ድጋፉ የአልጋ ፍራሽን ጨምሮ አንሶላ እና ብርድ ልብስን ያካተተ ሲኾን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበት ድርጅቱ አስታውቋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰላምይሁን ሙላት በዞኑ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ድጋፍ የሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለያዩ ሁኔታዎች ተፈናቅለው ምቹ ባልኾነ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል። በዞኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የገለጹት ኀላፊው ካለው መጠነ ሰፊ ችግር አኳያ ለድጋፍ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አብራርተዋል። ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ወደ መደበኛ የሕይዎት ዘይቤ ለመመለስ ጥረት እንደሚደረግ ነው የገለጹት። ወርልድ ቪዥን በአጋርነት እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል።
የወርልድ ቪዥን ፕሮጀክት አሥተባባሪ የኾኑት ከማል ጀማል የችግሩን ጥልቀት በመረዳት ድጋፎችን እያቀረቡ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ለሴቶች፣ ለሕጻናት እና ለሌሎችም ተጋላጭ የማኅበረሰብ ከፍሎች ቅድሚያ በመስጠት ፍትሃዊ የድጋፍ ክትትል እያደረጉ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።
በቀጣይም ከ1 ሺህ 500 በላይ ለሚኾኑ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች የቤት ቁሳቁስ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል። ያለውን መጠነ ሰፊ የችግር ተጋላጭነት በመገንዘብ ድርጅቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
በድጋፍ መርሐ ግብሩ የተገኙት የደባርቅ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሰለሞን ጌትነት ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው በወረዳው የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የወረዳው አሥተዳደር ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል። ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች በወረዳው እንደሚገኙ ነው የተናገሩት። ድጋፍ አሥተባባሪ ቡድን በማቋቋም እና ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል የማኅበረሰብ ክፍሎቹን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ሢሠሩ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።
በቀጣይም ካለው መጠነ ሰፊ ችግር አኳያ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል። የድጋፉ ተጠቃሚዎችም በበኩላቸው በተደረገላቸው እገዛ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል። የሚገኙበት አካባቢ ደጋማ የአየር ንብረት ያለው በመኾኑ የፍራሽ፣ የብርድ ልብስ እና አንሶላ ድጋፍ መደረጉ ችግሩን ለመቋቋም እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!