“የቀጣናው ተሰፋ ሰጭ የሕክምና ማዕከል”

8
ባሕር ዳር: መስከረም 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የካንሰር በሽታ የተዛቡ ህዋሶች ወይም ጤናማ ባልኾነ የሰውነት ህዋሶች (ሴሎች) ዕድገት የሚከሰት እና ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች የሚሠራጭ የበሽታ ዓይነት ነው፡፡
እነዚህ በፍጥነት የሚያድጉ ሴሎች እብጠቶችን ሊያስከትሉ እና የሰውነትን መደበኛ ተግባር ሊያዛቡ የሚችሉ ናቸው፡፡ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ካንሰር በዓለም ላይ ለሞት ከሚዳርጉ በሽታዎች አንዱ እና ግንባር ቀደሙ ነው። በኢትዮጵያም ብዙዎችን ለከፍተኛ ሞት እና ስቃይ እየዳረጉ ከሚገኙ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ እንደኾነ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። ከበሽታው አሳሳቢነት ባለፈ በሀገሪቱ የጨረር ሕክምና የሚሰጥባቸው አካባቢዎች ውስን መኾን ሌላኛው ፈተና ነው። በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ፣ በሐዋሳ፣ በጅማ እና በሀሮማያ የጨረር ሕክምና ሲሰጥ ቆይቷል። በተያዘው በጀት ዓመትም አምስተኛው የጨረር ሕክምና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ተጀምሯል። የጨረር ሕክምና በሆስፒታሉ መጀመር ለአካባቢው የሚኖረውን ፋይዳ ምን እንደሚመስል ታካሚዎችን እና በሆስፒታሉ የጨረር ማዕከሉን ኀላፊ አነጋግረናል።
በሆስፒታሉ የጨረር ሕክምና እየተከታተሉ ከሚገኙት ታካሚዎች ውስጥ ዋኘው አለባቸው አንዱ ናቸው። ታካሚው ለ15 ዓመታት ያህል በተለያዩ አካባቢዎች በጤና ባለሙያነት ማኅበረሰቡን አገልግለዋል። በርካቶችን ከሕመማቸው እንዲፈወሱ ሙያዊ ግዴታቸውንም ተወጥተዋል።
የብዙዎችን ሕይዎት የታደጉት የጤና ባለሙያ ከ2017 ዓ.ም ጥር ወር ጀምሮ ባጋጠማቸው ፕሮስቴት ካንሰር ምክንያት በክኒን እና በመርፌ የሚሰጥ መድኃኒት ሲወስዱ ቆይተዋል። ከቅር ጊዜ ጀምሮ ደግሞ የጨረር ሕክምና መጀመራቸውን ነው የገለጹት። አሁን ላይ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ታካሚው እንዳሉት የጨረር ሕክምና መጀመሩ ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች አካባቢዎች ይደረግ የነበረውን እንግልት አስቀርቷል ነው ያሉት። በተለይም ደግሞ ባለፉት ዓመታት በተከሰተው የጸጥታ ችግር በመንገድ መዘጋት፣ በምጣኔ ሃብት አቅም እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ የሕክምና ተቋማት ተጉዞ ለመመርመር ፈታኝ አድርጎት ቆይቷል፤ ብዙዎችም ለጉዳት ተጋልጠዋል ብለዋል።
አሁን ላይ ሕክምናው በጎንደር ሆስፒታል መሰጠቱ በርካታ ታካሚዎች በማዕከሉ ክትትል እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል ነው ያሉት። ሆስፒታሉ የተጀመሩ ግንባታዎችን ፈጥኖ በማጠናቀቅ እና የተሟላ ግብዓት በማሟላት የተማላ አገልግሎት እንዲሰጥም ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የካንሰር እና ጨረር ማዕከል ኀላፊ ዶክተር ኤፍሬም ታፈሰ የጎንደር ሆስፒታል የካንሰር ሕክምና መስጠት ከጀመረ 10 ዓመታትን ማስቆጠሩን ገልጸዋል። በሆስፒታሉ ከሚታከሙ የካንሰር ሕሙማን ውክጥ እስከ 60 በመቶ የሚኾኑት የጨረር ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ኾኖ በመገኘቱ ከ2018 በጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ የጨረር ሕክምና ተጀምሯል ነው ያሉት። ሕክምናው ከጀመረ ጀምሮም 80 የሚኾኑ ታካሚዎች አገልግሎቱን አግኝተዋል ብለዋል። ኀላፊው እንደገለጹት ሕክምናው በሆስፒታሉ መሠጠቱ የታካሚዎችን እና አስተማሚዎችን እንግልት ቀንሷን ብለዋል። ታካሚዎችም በአካባቢያቸው በጤና ኢንሹራንስ ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ ያልተገባ የሕክምና ወጭን እና ያልተፈለገ ጉዞን አስቀርቶላቸዋል ነው ያሉት። ይህም የታማሚዎችን የመዳን ዕድል ያሳድጋል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የካንሰር ጨረር ሕክምናን በተደራጀ መንገድ ለመሥጠት ትልልቅ ግንባታዎችን እያስገነባ መኾኑንም ገልጸዋል። ግንባታዎቹ ትላልቅ የተለያዩ የጨረር መመርመሪያ ማሽኖች የሚቀመጡበትን እና 194 የሚደርሱ አልጋዎችን እንደሚይዝም ነው የተናገሩት። የጨረር ሕክምናው ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ነዋሪዎች እና ለጎረቤት ሀገራት ጭምር አገልግሎት የሚሠጥ እንደኾነ ነው የገለጹት። ሆስፒታሉ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንዲገባ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። የጎንደር ሆስፒታል የካንሰር ጨረር ሕክምና በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የመጀመሪያ ሲኾን በኢትዮጵያ ደግሞ አምስተኛው ኾኖ ተቀምጧል። ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ብቸኛ የኾነው የሕጻናት ካንሰር ሕክምና በሆስፒታሉ እንደሚሰጥ ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየደመራ ችቦ ገበያው እና የበዓሉ ድምቀት።
Next articleምዘናን እያጠናከሩ ውጤታማ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሳሰቡ።