የደመራ ችቦ ገበያው እና የበዓሉ ድምቀት።

14
ባሕር ዳር፡ መስከረም 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል እና በዩኒስኮ የተመዘገበው የመስቀል ደመራ በዓል ልዩ ድምቀት ካላቸው በዓላት መካከል ይገኝበታል።
መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን እና የዘለዓለም ሕይወትን ለመስጠት መስዋዕትነት የከፈለበት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት መንበር እንደኾነ የሃይማኖቱ ተከታዮች ያምናሉ። ይህ መስቀል ታዲያ ረጅም ጊዜ ተቀብሮ ከነበረበት እና የቆሻሻ መጣያ ኾኖ ከኖረበት ቦታ ፈልጎ ለማውጣት ንግሥት ኢሌኒ ደመራ ደምራ ያደረገችውን ጥረት ተንተርሶ የሚከበር በዓል ነው የደመራ በዓል። በዚህ ወቅትም የመስቀሉ መገኘትን እና ብዙ ተአምራትን ማድረጉን ተንተርሶ ሰዎች ለንጉሱ ደስታቸውን ለመግለጽ ችቦ ይዘው እንደሄዱ በባሕር ዳር ከተማ የጽራ ጽዮን ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል መምህር ይትባረክ ደምለው ይገልጻሉ።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ታዲያ የመስቀል በዓል እና ችቦ ድርና ማግ ኾነው ዘመናትን ተሻግረዋል ነው የሚሉት መምህሩ።ችቦ የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮት መገለጥን የሚያመለክት ነውም ብለዋል፡፡ መስከረም 16 እና 17 የደመራ በዓል ሲከበር ዋነኛ የበዓሉ ማድመቂያ ችቦ ነው፡፡ ችቦ ትልቅ የተስፋ መገለጫ ነው፡፡ ተስፋ ደግሞ የደስታ ምንጭ ነው፡፡ በመኾኑም ችቦ ለኩሰን በዓሉን እናከብራለን፡፡
👉ለመኾኑ የችቦ ገበያው በዚህ ዓመት እንዴት ዋለ?
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የጨንታ ሦሥቱ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት ወይዘሮ ከተማየ ላቄ ችቦ ሲሸጡ አሚኮ ያገኛቸው እናት ናቸው። የያዙትን ችቦ እንደየ አካባቢው ስሙ እንደሚለያይ ገልጸው በነሱ አካባቢ ጠንቦራ እንደሚባል ነግረውናል። እንጨቱ ኩሸሽሌ ተብሉ ይጠራል ያሉት ወይዘሮ ከተማየ ላቄ ኩሸሽሌውን ለመሠብሠብ ራቅ ወዳለ ቦታ በመሄድ በጭንቅላታቸው ረጅም መንገድ ተሸክመው እንደሚያመጡት ተናግረዋል። እሳቸው የያዙት ጠንቦራ በበጋ ወራት ሲሠበሥቡት ከቆዩ በኋላ ለሽያጭ ሲያመጡት ርጥብ ኾኖ እንዳያስቸግር በክረምት ወቅት ዝናብ ከማያገኘው ቦታ እንደሚያስቀምጡት ገልጸዋል።
በየዓመቱ የመሸጥ ልምድ እንዳላቸው ነግረውናል። የዘንድሮው ገበያ ከአምናው በተለየ የዋጋ መቀነስ ይታይበታልም አሉን። የዚህ የጠንቦራ ሽያጭ በዓመት አንድ ጊዜ የመስቀል በዓልን ተከትሎ የሚያገኙት የገቢ ማግኛቸው እንደኾነም ገልጸዋል። “ጠንቦራውን እኔ የምሸጠው ለአንዳንድ የቤት ወጭ ስለሚያግዘኝ እና ከዓመት ዓመት ካደረስከኝ ብየ ስለትም ኑሮብኝ ነው” ሲሉ ለአሚኮ ገልጸዋል። የ55 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ አቶ ውድነህ ተሾመ በባሕር ዳር ዙሪያ ድልሽት ቀበሌ ነዋሪ ሲኾኑ ለመስቀል በዓል ችቦ ሲሸጡ አሚኮ ያገኛቸው አባት ናቸው። አቶ ውድነህ ተሾመ በአካባቢያቸው ይህ ችቦ ደቦት እየተባለ ይጠራል ይላሉ። አቶ ውድነህ ተሾመ ይህን ደቦት ለማዘጋጀት በበጋ ወራት ጀምረው ሲለፉ እና ሲደክሙ እንደነበርም ነግረውናል።
ከአሁን በፊት የደቦት ዋጋ ከዓመት ዓመት በእጥፍ አየጨመረ መምጣቱን በመግለጽ አሁን ላይ ግን ምክንያቱ ባልታወቀ ኹኔታ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ታይቶበታል ሲሉ ገልጸዋል። “ብዙ የለፋሁበት ደቦት ብዙ ወጭዎችን ይሸፍንልኛል ብየ አስቤ ባመጣውም አሁን ላይ በቅናሽ እየሸጥኩት ነው” ብለዋል። አንዱን ደቦት በስምንት ብር እየሸጡ መኾኑንም ተናግረዋል። ለበዓሉ ድምቀት እና ሃይማኖታዊ በዓል “የኛ ደቦት መሸጥ ትልቅ ሚና አለው” ብለዋል። የሰው ልጅ ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ብሩህ እና የተሻለ እንዲኾን ለመመኘት ሻጩም አስተያየት አድርጎ መሸጥ እንዳለበት እና ገዥውም ቢኾን ለበዓሉ ማድመቂያ ሲል ደቦት ሳይዝ ወደ ቤቱ መሄድ እንደሌለበት አቶ ውድነህ ተሾመ ገልጸዋል።
በተለያየ ቦታ የተለያየ መጠሪያ ያለው ችቦ እንደየ አካባቢው እና ቦታው መጠሪያው ቢለያይም በሃይማኖታዊ ይዞታው ግን ችቦ ተብሎ ነው የሚጠራው። ችቦ ለመስቀል በዓል የሚበራው አንድም በሃይማኖታዊ ይዘቱ እና በባሕላዊ አንድምታው ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች መስከረም 16 ማታ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ መስከረም 17 ጧት ‹‹የጎመን ምንቸት ውጣ! የገንፎ ምንቸት ግባ “እንጎሮገባሽን” ብለው ችቧቸውን በየቤታቸው ይለኩሳሉ፡፡ የቤታቸውን ምሶሶ፣ ጓዳ እና ዋና ዋና የሚባሉትን የቤት ዕቃዎች እንዲሁም የከብቶች ማጎሪያ በእሳት ይተኩሳሉ፡፡
በመቀጠል ቅርብ ለኾኑ ጎረቤቶች እና ወዳጅ ዘመዶች ቤት ይሄዱ እና ‹‹አንጎሮጎባሽ ለዓመቱ ያድርስህ ወይንም ያድርስሽ›› በማለት በችቦው ቤታቸውን እየነኩ ያላቸውን መልካም ምኞት እና ብሩህ ተስፋ ይገልጻሉ፡፡ ተቀባይ ቤተሰቦች ደግሞ ‹‹ አሜን ለከርሞው በሰላም በጤና ያድርሰን ›› በማለት የመልካም ምኞት መገለጫውን የተቀበሉት ስለመኾኑ ግብረ-መልስ ይሰጣሉ፡፡ የአካባቢው ሰው ይሄንን ካደረጉ በኋላ የለኮሱት ችቦ ሳይጠፋ የደመራ ሥነ-ሥርዓት ወደሚደረግበት ቦታ በደስታ ይሄዳሉ፡፡ ደመራ ያለበት ቦታ ደርሰውም በያዙት የሚነድ ችቦ በደስታ በፌሽታ ይደምቃሉ።
መልካም የመስቀል ደመራ በዓል!
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የቱሪስት መስህቦች አንድነትን እና መከባበርን ሊፈጥሩ ይገባል” ሰላማዊት ካሳ
Next article“የቀጣናው ተሰፋ ሰጭ የሕክምና ማዕከል”