
ሁመራ፡ መስከረም 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀልን በዓል ከዋዜማው እስከ በዓሉ ድረስ ኅብረተሰቡ ያለጸጥታ ችግር ማክበር እንዲችል የተቀናጀ የጸጥታ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
ፖሊስ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከዞኑ ሰላም አስከባሪ ኃይል እና ከሚሊሻ ጋር በመቀናጀት በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የፖሊስ መምሪያው አዛዥ ኮማንደር ወለላው ተገኘ ገልጸዋል። መስቀል በድምቀት የሚከበር ታላቅ በዓል መኾኑን ያነሱት ኮማንደር ወለላው ከደመራ መለኮስ ጋር ተያይዞ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
በዓሉ በሚከበርባቸው አደባባዮችም ኾነ በየትኛውም የዞኑ አካባቢ ርችት፣ ሮኬት፣ ጥይት እና ማንኛውም አይነት ተቀጣጣይነት ያላቸውን ነገሮች መጠቀም መከልከሉን አስረድተዋል። ለዚህ ቁጥጥር እና ክትትል ይመች ዘንድም በቀበሌ፣ በወረዳ እና በዞን ደረጃ ከሁሉም የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ስምሪት መሰጠቱን ኮማንደር ወለላው ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ የሰላሙ፣ የጸጥታው እና የበዓሉ ባለቤት በመኾኑ የአካባቢውን ደኅንነት ለማረጋገጥ ከዚህ በፊት የነበረውን ንቁ ተሳትፎ በመስቀል በዓል አከባበር ላይ እንዲያስቀጥልም ጥሪ አስተላልፈዋል።በአካባቢው ከሚገኙ የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀትም ትክክል ያልኾኑ ምልክቶች ሲስተዋሉ ጥቆማ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮችም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!