
ፍኖተ ሰላም: መስከረም 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የበቆሎ ሰብል በስፋት ከሚመረትባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ውስጥ የምዕራብ ጎጃም ዞን ቀዳሚ ነው። በዞኑ ከመደበኛው የሰብል ልማት በተጨማሪ የበቆሎ ዘር ብዜትም በሰፊው ይከናወናል።
አቶ አለሙ በላይ በቡሬ ዙሪያ ወረዳ ደንቡን ቀበሌ የሚኖሩ አርሶ አደር ናቸው። በአካባቢው በቆሎ የተለመደ የሰብል ምርት መኾኑን እና ከዚህ በፊት በቆሎ በማምረት ከአንድ ሄክታር በአማካይ ከ70 ኩንታል በላይ ምርት ያገኙ እንደነበር ነግረውናል። በዚህ ዓመት ከአንድ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ ሰብል መሸፈናቸውንም ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ ግማሽ ሄክታር የሚኾነው በበቆሎ ዘር ብዜት የተሸፈነ ሲኾን አሁን ላይ ጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ከዚህም ከሄክታር 80 ኩንታል በቆሎ ምርት እንደሚጠብቁ ነው የተናገሩት። በዚሁ ወረዳ አርሶ አደር የኾኑት አቶ አዲስ በቀለ ደግሞ 2 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት በበቆሎ መሸፈናቸውን ተናግረዋል። በዚህ ዓመት ያለው የበቆሎ ቁመና ከወትሮው የተለየ በመኾኑ የተሻለ ምርት ተስፋ እንዳደረጉ ገልጸውልናል።
በቡሬ ዙሪያ ወረዳ በምርት ዘመኑ ከ26 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በበቆሎ ሰብል መሸፈኑን የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙላት አዲስ ናቸው። ከ16 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በክላስተር የተሸፈነ እንደኾነም ገልጸዋል። በወረዳው ከለማው አጠቃላይ የበቆሎ ሰብል ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። በምዕራብ ጎጃም ዞን በ2017/18 የምርት ዘመን ከጥቅል ምርቱ ላይ በቆሎ 45 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝም ነው የተናገሩት።
በዚህም ከ122 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በበቆሎ መሸፈኑን እና 98 ሺህ ሄክታር የሚኾነው ደግሞ በክላስተር የተዘራ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አጉማሴ አንተነህ ናቸው። በዞኑ ውስጥ በ12 ቀበሌዎች 1ሺህ 392 ሄክታር መሬት በበቆሎ ዘር ብዜት የተሸፈነ መኾኑንም ገልጸዋል።በዞኑ አጠቃላይ ከተሸፈነው በቆሎ ሰብልም ከ8 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ነው የመምሪያ ኀላፊው የተናገሩት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!