
ወልድያ: መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የባሕር ጥያቄ የሕዝብ እና የመንግሥት አጀንዳ ኾኗል።
በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ማብሬ ታዴ ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ዘመናት የባሕር በር ባለቤት በመኾኗ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ተቋቁማ ማለፍ አስችሏታል ብለዋል። በተለይም በቀዝቃዛው ጦርነት ኢትዮጵያ በወቅቱ የባሕር በር ባለቤት መኾኗ ከጉዳት እንደታደጋት አውስተዋል። በአጼ ኀይለ ሥላሴ ዘመንም የኢትዮጵያ ባሕር ኀይል አሰብ ላይ ወታደራዊ መሰረት ስለነበረው ከምዕራባውያን ጋር ፍትሐዊ ግንኙነት እንዲኖር አቅም ፈጥረዋል ነው ያሉት። የባሕር በር አለመኖር የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ስጋት ነው ያሉት መምህሩ ኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታት የጆኦ ፖለቲካ እስረኛ ኾና ከባሕር በር ርቃ በመቆየቷ የችግሩ ሰለባ ኾና ቆይታለች ብለዋል።
ለዚህም የባሕር በር ያላቸው ጎረቤት ሀገራት እና የኢትዮጵያ የሸቀጥ ዋጋ ልዩነት መኖሩን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ የወደብ ኪራይ ስለሚኖርባት በሸማቹ ላይ ወጋ ጭማሪ ይደረጋል፤ በተመሳሳይ የሸቀጥ በወቅቱ አለመድረስም ያጋጥማል ነው ያሉት። ለደኅንነትም ስጋት ነው፤ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እና የጦር መሳሪያዎች በሌሎች ሀገር ሲያልፍ ምሥጢራዊ ደኅንነቱ ይባክናል ያሉት መምህሩ ኢትዮጵያ የራሷ ባሕር በር ቢኖራት ማንኛውም ግብይት እና ወታደራዊ መሳሪያ እንቅስቃሴ ምሥጥራዊ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንደሚኾን አንስተዋል። አሁን ላይ ኢትዮጵያ የምታነሳው የባሕር በር ጥያቄም ፍትሐዊ መኾኑን ገልጸዋል።
እንደ ማሳያ የጠቀሱትም ኢትዮጵያ ያላት የሕዝብ ብዛት፣ በቀጣናው ያላት ሚና እና ለቀይ ባሕር ወደብ ያላት ቅርበት የባሕር በር እንዲኖራት ግድ የሚሉ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል። በተለይም ቀይ ባሕር የዓለም ንግድ እንቅስቃሴ በስፋት የሚሳለጥበት ቀጣና በመኾኑ እና ወታደራዊ ጠቀሜታው ጉልህ በመኾኑ በአስር ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያሉ እንደ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ፈረንሳይ እና መሰል ኀያላን ሀገራት ቀይ ባሕር ላይ ወታደራዊ መሰረት አላቸው። ኢትዮጵያ ደግሞ በቅርብ ርቀት ላይ ኾና ራሷን ለመጠበቅ እና በቀጣናው ላይ የራሷን ሚና እንድትጫወት የሚያስችል መሰረት እንዳይኖራት መከልከል ተግቢ እንዳልኾነ አስረድተዋል። ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ እና በዲኘሎማሲ ሊፈታ እንደሚገባም መክረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን