የዲዛይን እና የጥናት ሥራዎችን በወቅቱ እና በጥራት ለማከናወን ትኩረት ተደርጓል።

9
ባሕር ዳር: መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የልህቀት፣ ዲዛይን እና ቁጥጥር ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምን እየገመገመ ነው።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አብርሃም አያሌው ኮርፖሬሽኑ በክልሉ ውስጥ በመጠጥ ውኃ፣ በመስኖ ዲዛይን፣ በከተማ ፕላን፣ በመንገድ፣ በድልድይ እና በሕንጻ ግንባታ ላይ የዲዛይን ጥናት ማማከር ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ከክልሉ ውጭም አራት ክልሎች ላይ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት። ኮርፖሬሽኑ በ2017 በጀት ዓመት 330 ፕሮጀክቶች ላይ የዲዛይን እና የማማከር ሥራ ላይ ተሳትፏል ብለዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 72 በመቶ የሚኾኑትን መፈጸም ተችሏል። እንደ መገጭ፣ አጅማ ጫጫ፣ የሽንፋ መስኖ ፕሮጀክት፣ የባሕር ዳር የኮሪደር ልማት እና በዞን ከተሞችም የተሠሩ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ከተሠሩት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።
ኮርፖሬሽኑ እያከናወነ የሚገኘው ሥራ ከክልሉ አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተጀመረው ልማት አቅም መኾኑንም ገልጸዋል። ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲኾኑ በፕሮጀክቶቹ አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። በተያዘው በጀት ዓመትም የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው ጊዜ በጥራት ለማከናወን ትኩረት ተሠጥቷል ነው ያሉት ሥራ አሥፈጻሚው።
በኮርፖሬሽኑ የአፈር እና መሬት ተስማሚነት ጥናት ፕሮጀክት ማናጀር ታደሰ መኮንን ባለፈው በጀት ዓመት የመካከለኛ መስኖ ፕሮጀክትን የጥናት መረጃ የመሠብሰብ ሥራ አንዱ ትኩረት እንደነበር ገልጸዋል። ከዚህ በፊት ተጀምረው የነበሩ ከፍተኛ የመስኖ ፕሮጀክት ሥራዎች ጥናትም ትኩረት የተሠጠው ጉዳይ እንደነበር ተናግረዋል።
በኮርፖሬሽኑ የሕንጻ እና ከተማ ፕላን ጥናት እና ዲዛይን ቡድን ተወካይ ኀላፊ የኾኑት አቤል አየለ በ2017 በጀት ዓመት የህንጻ ውበትን ከማስጠበቅ ጀምሮ ትልልቅ የዲዛይን ሥራዎችን መሥራት እንደተቻለ አንስተዋል። ከዚህ ውስጥ እንደ ሰሜን ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ፍትሕ መምሪያ የዲዛይን ሥራዎችን ማጠናቀቅ መቻሉን በማሳያነት ተናግረዋል። የሚሠሩ ግንባታዎች ምቹ፣ ሳቢ እና ማራኪ ማድረግ እና ቴክኖሎጅ ጭምር የማካተት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት። በቀጣይ የሚሠሩ ግንባታዎችም ሥራን የሚያቀላጥፉ እና ወቅቱ የደረሰባቸውን ቴክኖሎጅዎች በማካተት ለመሥራት ጥረት ተደርጓል ብለዋል። ኮርፖሬሽኑ ከተመሠረተ ጀምሮ ከ3 ሺህ 400 በላይ በሚኾኑ ፕሮጀክቶች ላይ የዲዛይ እና የማማክር ሥራዎችን ማከናወን እንደተቻለም በዕለቱ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ወደብ አልባ ኾኖ ታላቅ የኾነ ሀገር የለም” ጋዜጠኛ ግሬጎሪ ኮፕሌይ
Next articleየባሕር በር የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ዋስትና ማረጋገጫ ነው።