የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታወቀ።

11
ገንዳ ውኃ፡ መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በመላው የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ምሥጋናው ካሴ ተናግረዋል።
በአደባባይ ከሚከበሩ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ በዓል አንዱ መኾኑን አንስተው ከበዓሉ ዋዜማ አንስቶ እስከሚጠናቀቅበት ድረስ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።
በአደባባይ በዓሉም ማኅበረሰቡን የሚያስደነግጡ ድምጽ ያላቸው ተተኳሽ ነገሮች እንዳይተኮሱ እና ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ እየተሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል። በበዓል ወቅት ከፍተኛ ግብይት ስለሚከናወን በዚህ ሰዓት የሃሰተኛ ብር ኖት ስለሚበዛ ማኅበረሰቡ እንዲጠነቀቅ እና ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እንዲሰጥም ኮማንደር ምሥጋናው ካሴ አሳስበዋል።
ማኅበረሰቡ በዓሉን ተንተርሶ ከሚደረጉ የሰዓት እላፊ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ በአልኮል ግፊት ከሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራት ራሱን መጠበቅ እንዳለበት ተናግረዋል። ወጣቶች በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ትብብር እና እገዛ ማድረግ እንዳለባቸውም ተጠቁሟል። ለመላው የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታይ በሙሉ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ኮማንደሩ አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበ2018 የተሻለ ግብር ለመሠብሠብ በትኩረት እየሠራ መኾኑ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።
Next article“ወደብ አልባ ኾኖ ታላቅ የኾነ ሀገር የለም” ጋዜጠኛ ግሬጎሪ ኮፕሌይ