በ2018 የተሻለ ግብር ለመሠብሠብ በትኩረት እየሠራ መኾኑ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።

8
ባሕር ዳር: መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ግብር የመንግሥትን ገቢ ከፍ በማድረግ የዜጎችን የመሰረተ ልማት ፍላጎት ምላሽ በመስጠት የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚጠቅም የአንድ ሀገር የደም ስር ነው፡፡
ግብር ከእያንዳንዱ የንግዱ ማኅበረሰብ የየዕለት እንቅስቃሴ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ጠቀሜታዎቹም ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡
ለማኅበራዊ አገልግሎት መስፋፋት፣ ለባሕል እድገት፣ ለሀገር ደኅንነት፣ ለፍትሕ እና ለመልካም አሥተዳደር በአንድም በሌላ መንገድ ግብር አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ ሰላም ሲኖር ግብር በተሻለ ይሰበሰባል፡፡ ልማቱም በተሻለ ኹኔታ ይቀጥላል፡፡
ይህንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ እና በጊዜው ያለማንም አስገዳጅነት ክፍያቸውን የሚፈጽሙ ግለሰቦች ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ከነዚህ ግብር ከፋዮች መካከል በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኙ ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን በልብስ ስፌት እና በብትን ጨርቅ ንግድ የተሰማሩ ግለሰብ እና የመድኃኒት መሸጫ መደብር ነጋዴዎችን አነጋግረናል፡፡
ነጋዴዎቹ ግብራቸውን ያለምንም አስገዳጅ ኹኔታ በአግባቡ መክፈል መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም እንደ ዜጋ ለሀገራችን የሚጠበቅብንን ግዳጅ እንደተወጣን ይሰማናል ነው ያሉት፡፡ በቀጣይም ግብራቸውን ወቅቱን ጠብቀው እንደሚከፍሉ እና ለሌሎች ግብር ከፋዮች አርዓያ እንደሚኾኑ ነው የተናገሩት፡፡
በደብረ ማርቆስ ከተማ የበጀት ዓመቱ የደረጃ “ሐ” የግብር አፈጻጸም የተሻለ እንደነበር የተናገሩት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው አለበል ናቸው፡፡
በበጀት ዓመቱ ከንግዱ ማኅበረሰብ እና ከኪራይ ግብር ከፋዮች 56 ሚሊዮን 269 ሺህ 922 ብር መሠብሠብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ይህም በበጀት ዓመቱ ለመሠብሠብ ከታቀደው 111 ነጥብ 7 በመቶው መፈጸም ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በቀጣይም ገቢ የመሠብሠብ ተግባር የሁሉንም ተቋማት እና የበርካታ አጋር አካላትን ርብርብ የሚጠይቅ በመኾኑ ቅንጅታዊ አሠራርን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከ455 ሺህ 410 የደረጃ “ሐ” የንግዱ ማኅበረሰብ እና ከኪራይ ገቢ ግብር ከፋዮች 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ታዘባቸው ጣሴ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም የገቢ አሠባሠብ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መሠብሠብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መፈጸሙንም ነው የተናገሩት፡፡ በቀጣይም በዘመናዊ መንገድ ግብር የመሠብሠብ ሥራን በማጎልበት የግብር አሠባሠብ ሥርዓትን በመከተል እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
በ2018 የግብር አሠባሠብን ውጤታማ ለማድረግም ግብር የምከፍለው ለልማት ነው በሚል አስተሳሰብ ግብሩን ደስተኛ ኾኖ እንዲከፍል “ግብሬን ደስ ብሎኝ እከፍላለሁ” በሚል የንቅናቄ መድረክ በማዘጋጀት ለግብር ከፋዩ የግንዛቤ ፈጠራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየመስቀል በዓል በሰላም እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next articleየመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታወቀ።