
ደብረ ማርቆስ፡ መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የመስቀል በዓል ሰላማዊ በኾነ መልኩ እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ማከናወኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
የመምሪያው ኀላፊ ኮማንደር ቢምረው አሰፋ ለአሚኮ እንደገለጹት ከሃይማኖት አባቶች፣ ከወጣቶች እና ከጸጥታ አካላት ጋር በመመካከር በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል። የመስቀል በዓል ትልቅ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓል መኾኑን ያነሱት መምሪያ ኀላፊው ኅብረተሰቡ ደመራ በሚለኮስበት ጊዜ እና ከኤሌክትሪክ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ እና ኀላፊነት በተሞላበት መልኩ ተግባራትን እንዲያከናውን አሳስበዋል።
የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል ኅብረተሰቡ የእግረኛ መተላለፊያ መስመሮች ላይ ደመራ ባለመደመር ተባባሪ እንዲኾንም ጥሪ አቅርበዋል። ርችት እና መሰል ተቀጣጣይ ነገሮችን ከማፈንዳት መቆጠብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ኅብረተሰቡ ከጸጥታ ኀይሎች ጋር በመተባበር በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ኀላፊነት እንዲወጣ እና ችግሮች ሲያጋጥሙ ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም መልዕክት አስተላልፈዋል።ለመላው የክርስት ሃይማኖት ተከታዮችም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!