በበጀት ዓመቱ ችግር ፈች የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ተሠርተዋል።

2
ደባርቅ፡ መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ አካሂዷል። የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጌትነት ጸጋዬ የከተማውን ሰላም እና ጸጥታ ለማሻሻል የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የጸጥታ መዋቅሩን አደረጃጀት በማሻሻል ተልዕኮ የመፈጸም አቅሙን ከፍ ለማድረግ ተሞክሯልም ብለዋል። የከተማውን ሰላም እና ጸጥታ ለማሻሻል በተደረጉ ጥረቶች ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት መቻሉንም ገልጸዋል። የማኅበረሰቡ ሚናም ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።
የተለያዩ ችግር ፈች የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች መከናዎናቸውን የገለጹት ከንቲባው ይሄም ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት እና ቅልጥፍና በኩል የታዩ ክፍተቶችን ለማረም ጥረት እንደሚደረግም ነው ያብራሩት።
በብልጽግና ፓርቲ የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደራጀው ባዘዘው ከማኅበረሰቡ ጋር በቅርበት ለመሥራት የሚያስችሉ ውጤታማ የሕዝብ ግንኙነት ተግባራት መከናዎናቸውንም ገልጸዋል። የሕዝብ ግንኙነት ሥራው መጠናከር ዋና ዋና የማኅበረሰብ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት ዕድል መፍጠሩንም አብራርተዋል። በትምህርት፣ በጤና፣ በንግድ እና ገበያ ልማት ዘርፎች አበረታች ተግባራት መከናዎናቸውንም ጠቅሰዋል። በቀጣይም ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና ለማርገብም በትኩረት እንደሚሠራ ነው የጠቆሙት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article”ደብተር እየተሰጠኝ እንዴት እኔ ተኝቼ አድራለሁ?” ድጋፍ የተደረገለት ተማሪ
Next articleየመስቀል በዓል በሰላም እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።