”ደብተር እየተሰጠኝ እንዴት እኔ ተኝቼ አድራለሁ?” ድጋፍ የተደረገለት ተማሪ

34
ባሕር ዳር: መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ ለመደገፍ በሚደረገው ዘመቻ ተቋማት ድጋፋቸውን ቀጥለዋል።
የዓባይ የሕትመት እና የወረቀት ፓኬጅንግ ፋብሪካ፣ ዴቨሎፕመንት ኤክስፐርቲስ ሴንተር (ዴክ) እና የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለተማሪዎች ድጋፍ አድርገዋል። የድጋፉ ተጠቃሚ ተማሪ ገበያው ዋለ የተደረገለት የደብተር ድጋፍ ትምህርቱ ላይ እንዲያተኩር እንደሚያደርገው ገልጿል። ”ደብተር እየተሰጠኝ እንዴት እኔ ተኝቼ አድራለሁ?” በማለት ጠንክሮ እንደሚያጠና ነው የተናገረው። የዓባይ ሕትመት እና ወረቀት ፓኬጂንግ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ታደሰ ሽመላሽ ተቋማቸው ድጋፉን ለሦስተኛ ጊዜ ማድረጉን ገልጸዋል። ለትምህርት ዘመኑ 65 ሺህ ደብተር ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በክልሉ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። የአንደኛ እና ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ለመገንባትም ለባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የቦታ ጥያቄ ማቅረቡን ተናግረዋል። በዴቨሎፕመንት ኤክስፐርቲስ ሴንተር (ዴክ) የአማራ ክልል አስተባባሪ ዓይናለም ታፈረ ድርጅታቸው 65 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በክረምቱ የሰብዓዊ ሥራዎች ዘመቻ የተለያዩ ሰው ተኮር ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥም አንዱ ተማሪዎችን በቁሳቁስ መደገፍ ነው ብለዋል። በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ለመማር የሚቸገሩ ሕጻናትን ለመደገፍ የተጀመረው ንቅናቄ ዓመታትን እያስቆጠረ መኾኑን ገልጸዋል። የመማሪያ ቁሳቁስ ሰብስበን ለተማሪዎች ስንሰጥ ትውልዱ ላይ በመሥራት ነገን የተሻለ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየሚፈለገውን ዕድገት ለማምጣት ሰላምን በማረጋገጥ ለጋራ ሕልም በጋራ መሥራት ይገባል።
Next articleበበጀት ዓመቱ ችግር ፈች የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ተሠርተዋል።