የሚፈለገውን ዕድገት ለማምጣት ሰላምን በማረጋገጥ ለጋራ ሕልም በጋራ መሥራት ይገባል።

4
ደብረብርሃን፡ መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን እና በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በሰላም እና ጸጥታ ዙሪያ ያተኮረ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሂዷል፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በቀጣናው ሕግን ከማስከበር ተልዕኮ ባሻገር በልማታዊ ሥራዎች አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ በቀጣይም የሚተገበር ተልዕኮ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡
“የምንፈልገውን ዕድገት ለማምጣት ከሰላም እና ልማት መንገዶቻችን ላይ የሚገድቡ መሰናክሎችን በማራቅ ለጋራ ሕልም በጋራ መሥራት ይጠይቃል” ብለዋል፡፡
የተቋማትን የመፈጸም አቅም በማሳደግ አገልግሎት አሰጣጥን ማሳለጥ ላይ በትኩረት በመሥራት የሕዝብን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የቀጣዩን ትውልድ ለመገንባት የተጀመሩ የኢትዮ ኮደርስ፣ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ እና የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አበባው ሰይድ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና መላው የጸጥታ መዋቅር ከሕዝብ ጋር በመኾን ያመጣውን ሰላም ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ማኅበረሰቡም ከዚህ በፊት በግጭት ምክንያት ከደረሰው ውድመት በመማር በቀጣይ ሰላምን ለማጽናት በቁርጠኝነት መሠራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የታጠቁ ኀይሎች ሰላማዊ ከኾኑ አማራጮች ውጭ ፍላጎትን በትጥቅ ትግል ማስፈጸም እንደማይቻል በማመን ከዚህ አክሳሪ መንገድ በመነጠል ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ አሳስበዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት በዞኑ ሰላምን ለማረጋገጥ በትኩረት ሢሠራ እንደነበር ያስታወሱት የሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ ለሰላም ቅድሚያ የሰጡ አካባቢዎች ወደ ልማት ገብተዋል ብለዋል፡፡
በቀጣይም የዞኑን የጸጥታ መዋቅር በማጠናከር ሕዝቡም የድርሻውን እንዲወጣ ይሠራል ነው ያሉት።
የመጣውን ሰላም በዘላቂነት ማስቀጠል፣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን የማስፋት የቀጣይ ትኩረት መኾኑን አብራርተዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የኢንዱስትሪ ከተማ የኾነችውን ደብረ ብርሃን ሰላሟን በማስጠበቅ ዕድገቷን ማስቀጠል ዋነኛ ሥራ መኾኑን ገልጸዋል።
ነዋሪዎች እና በከተማዋ የሚገኙ የጸጥታ አካላት ተቀናጅተው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየሠሩ መኾኑንም አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleመንግሥት ዓለም አቀፍ መርሕን ተከትሎ የባሕር በር ጥያቄን ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት አበረታች ነው።
Next article”ደብተር እየተሰጠኝ እንዴት እኔ ተኝቼ አድራለሁ?” ድጋፍ የተደረገለት ተማሪ