
ደባርቅ: መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ያነሳችው የባሕር በር የጋራ ተጠቃሚነት ጥያቄ ፍትሃዊ እና መርህን የተከተለ መኾኑን አሚኮ ያነጋገራቸው በሰሜን ጎንደር ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የነበራትን የባሕር በር በታሪክ አጋጣሚ ብታጣም ሕጋዊነትን መሠረት ባደረገ መልኩ የባሕር በር የማግኘት መብቷ ግን የተጠበቀ ነው ብለዋል።
የደባርቅ ከተማ ነዋሪ የኾኑት አቶ ይሁኔ ያዜ የባሕር በር ተጠቃሚነት ሀገሪቱ ያላትን ዓለም አቀፍ ግንኙነት በማሻሻል የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በቀጣናው ያለውን አሁናዊ የኃይል አሰላለፍ ለመዋጀት እና ብሔራዊ ደኅንነትን ለማስጠበቅ የባሕር በር ጥቅሙ ጉልህ መኾኑንም አክለዋል።
ሌላኛው የደባርቅ ከተማ ነዋሪ አቶ አዲስ መልኬ የባሕር በር ተጠቃሚነት የተሳለጠ የንግድ ሥርዓት ለመዘርጋት እና ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚጠቅም አብራርተዋል።
አብዛኞቹ ሸቀጦች የሚጓጓዙት በባሕር ትራንስፖርት በመኾኑ በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ ያለውን የኑሮ ውድነት እና የሸቀጦች የዋጋ ንረት ለማስተካከል የባሕር በር ተጠቃሚነት ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
የዳባት ወረዳ ነዋሪ የኾኑት ወይዘሮ ዘርፌ ምኅረት እንደገለጹት እንደ ኢትዮጵያ ላለች በርካታ የሕዝብ ቁጥር ላላት ታሪካዊ ሀገር የባሕር በር ተጠቃሚነት ጉዳይ የሕልውና ጉዳይ ነው።
የባሕር በር ተጠቃሚነት ጉዳይ በሰጥቶ መቀበል መርሕ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ እና የቀጣናውን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ አንስተዋል።
የዳባት ከተማ ነዋሪ አቶ ክፍሌ አቡሃይ በበኩላቸው የባሕር በር ጥያቄ አሁን ድንገት የተነሳ ጉዳይ ሳይኾን ለዓመታት ሲጠየቅ የነበረ ጥያቄ መኾኑን አስታውሰዋል። ስለኾነም ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንጻር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል።
መንግሥት ዓለም አቀፍ መርህን ተከትሎ የባሕር በር ጥያቄን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉም ነው የተናገሩት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን