ትምህርት አቋርጠው የከረሙ ተማሪዎች ለመማር መዘጋጀታቸውን ገለጹ።

5
ባሕር ዳር፡ መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል በገጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ከርመዋል። እነዚህ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠው በመክረማቸው በእጅጉ መቆጨታቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል። አሁን ለመማር ራሳቸውን ማዘጋጀታቸውን በመጠቆም።
ተማሪ መስከረም ውድነህ ትምህርታቸውን አቋርጠው ከከረሙ ተማሪዎች መካከል አንዷ ነች። አሚኮ ይህችን ተማሪ ለመስቀል በዓል የሚኾን ችቦ ስትሸጥ ነው ያገኛት። ችቦ ሽጣ በምታገኘው ገንዘብም የትምህርት ቁሳቁስ ገዝታ እንድምታስቀምጥም ተናግራለች። መስከረም በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የጨንታ ሦሥቱ ቀበሌ ነዋሪ እንደኾነችም ትገልጻለች። በጨንታ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እንደነበረች ነገረችን።
ይሁንና ክልሉ በገጠመው የጸጥታ ችግር የተነሳ ትምህርት አቋርጣ መክረሟን ጠቁማለች። “ትምህርት እንደ ጀመርኩ አስቀጥየው ቢኾን በዚህ ዓመት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እኾን ነበር ” ነው ያለችው። ታዳጊዋ ተምራ መምህር በመኾን ወላጆቿን የመደገፍ ሃሳብ እንደነበራትም ነግራናለች። ወደፊትም ያቋረጠችውን ትምህርት በመቀጠል መምህር ለመኾን የትምህርት ግብዓት እያሟላች ትገኛለች። አሁን ላይም ከብት በመጠበቅ እና እንጨት እየለቀመች በመሸጥ ጊዜዋን እያሳለፈች እንደኾነም ተናግራለች።
አሚኮም “ትምህርት ቤት እኮ ተከፍቷል። ለምን ተመዝግበሽ አትማሪም ?” ሲል ጠይቋታል። እሷም ወላጆቿ ከመስቀል በኋላ ሁኔታውን አረጋግጠው እንደሚያስመዘግቧት ነው የተናገረችው። ሌላው ተማሪ አበበ ጸጋዬ ይባላል። የመርዓዊ ከተማ ነዋሪ ነው፡፡ በ2016 የትምህርት ዘመን የ10ኛ ክፍል ተማሪ እንደነበርም አስታውሷል። ሰላማዊ አካባቢዎች የሚኖሩ የእርሱ የክፍል አቻዎቹ ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለመውሰድ እየተዘጋጁ መኾናቸውን ሲያስብ ከፍተኛ ቁጭት እንደሚፈጥርበት ነው የተናገረው፡፡
የደረጃ ተማሪ ነበርኩ የሚለው ተማሪ አበበ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ ተመዝግቦ ትምህርት መጀመሩን ተናግሯል። በአግባቡ ተምሮም የቴክኖሎጂ ሰው ለመኾን ራዕይ ሰንቋል። የሰሜን ሜጫ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተዋቸው በቀለ በወረዳው ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ትምህርት ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ በ2016 ዓ.ም መማር የነበረባቸው 91 ሺህ 140 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ከርመዋል ነው ያሉት፡፡ ለ2018 የትምህርት ዘመን ክረምት ላይ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን የመጠገን፣ የመማሪያ አካባቢን ምቹ የማድረግ፣ ለመምህራን የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት፣ ሕዝባዊ ንቅናቄ እና ቁጭት በመፍጠር አሁን ላይ በበርካታ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ተጀምሯል ነው ያሉት።
በተለያዩ ምክንያቶች ያልተመዘገቡ ተማሪዎች እንዲመዘገቡም በጋራ በመቀስቀስ ምዝገባው ተጠናክሮ መቀጠሉን ኀላፊው ተናግረዋል።
የሰሜን ጎጃም አሥተዳደር ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ የሺወርቅ ድረስ በዞኑ በርካታ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው በካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ማሳለፋቸውን አስታውሰዋል። ምክትል መምሪያ ኀላፊዋ በ2018 የትምህርት ዘመን ወላጆች ልጆቻቸው ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው በመክረማቸው ከፍተኛ ቁጭት ስላሳደረባቸው ዘንድሮ ትምህርት ቤቶች መዘጋት የለባቸውም በሚል ቀናዒ አስተሳሰብ ልጆችን አስመዝግበው እያስተማሩ ይገኛሉ። ምዝገባው መቀጠሉንም ምክትል ኀላፊው ተናግረዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኀበራዊ ዘርፍ እሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በ2016 የትምህርት ዘመን 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለማስተማር ቢታቀድም 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚኾኑት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አለመምጣቸውን አስታውሰዋል። በ2017 ዓ ም ደግሞ ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ታቅዶ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ሙሉነሽ 4 ሚሊዮን የሚኾኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መምጣት አልቻሉም። ከተመዘገቡት ተማሪዎች መካክልም ብዙዎቹ አቋርጠው መክረማቸውን ተናግረዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን ታዲያ ባለፉት ዓመታት ከትምህርት ገበታ ርቀው የነበሩ ተማሪዎችን በማካተት 7 ሚሊዮን 445 ሺህ 545 ተማሪዎችን ለማስተማር ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ መኾኑን ነው ቢሮ ኀላፊዋ ያመለከቱት፡፡ ከነሐሴ አጋማሽ 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገ ርብርብ 3 ሚሊዮን ያክል ተማሪዎች መመዝገባቸውን ነው ዶክተር ሙሉነሽ የተናገሩት። አሁንም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤታቸው እንዲመለሱ ሁሉም መረባረብ እንደሚገባው አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article”ዛሬ አግዘን ያስተማርናቸው ልጆች ነገ ሀገር እንዲያግዙ የቤት ሥራ እየሰጠናቸው ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next articleመንግሥት ዓለም አቀፍ መርሕን ተከትሎ የባሕር በር ጥያቄን ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት አበረታች ነው።