”ዛሬ አግዘን ያስተማርናቸው ልጆች ነገ ሀገር እንዲያግዙ የቤት ሥራ እየሰጠናቸው ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

4
ባሕር ዳር፡ መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ከሠራተኞቹ በተሠበሠበ ገንዘብ የገዛውን የትምህርት ቁሳቁስ ለትምህርት ቢሮ አስረክቧል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴም (ዶ.ር) ድጋፉን ተረክበዋል።
ድጋፉ ከተደረገላቸው መካከል በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የፊታውራሪ ሃብተማርያም ትምህርት ቤት ተማሪ ገበያው ዋለ የተደረገለት የደብተር ድጋፍ ትምህርቱ ላይ እንዲያተኩር እንደሚያደርገው ገልጿል። ቤተሰቦቹም ከጭንቀት እንደሚድኑ ነው ያስረዳው። በተሰጠው ደብተር ጠንክሮ በመማር ከራሱ አልፎ ሀገር ለማኩራት መዘጋጀቱንም አስረድቷል። ሌላዋ የድጋፉ ተጠቃሚ ተማሪ ዓመትበዓል ታደለ አሚኮ ባደረገላት የደብተር እና እስክርቢቶ ድጋፍ ተምራ ውጤታማ ለመኾን እንደምትተጋ ተናግራለች።
የአሚኮን ሠራተኞች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ያስረከቡት የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አማካሪ ግዛቸው ሙሉነህ አሚኮ የ”አንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ” ንቅናቄ ተሳታፊ መኾኑን ገልጸዋል። ንቅናቄው ባለፉት ሁለት ዓመታት በትምህርት ላይ የገጠመውን ችግር ለመፍታትም አጋዥ መኾኑን አንስተዋል። በትምህርት ዘርፉ ላይ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ አስፈላጊነትም ጠቅሰዋል። ሠራተኞቹ እንደ ዜጋ ኀላፊነታቸውን ከመወጣታቸውም በላይ አሚኮም እንደ ተቋም ትምህርትን አጀንዳ አድርጎ በመሥራት ኀላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል። በቀጣይም በትምህርት ንቅናቄው በግንባር ቀደምትነት እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
በየዞኑ የሚገኙ የአሚኮ ቅርንጫፍ ሠራተኞችም በየአካባቢው ለሚገኙ ተማሪዎች ተመሳሳይ ድጋፍ አድርገዋል ነው ያሉት። ድጋፉን ተረክበው መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴም (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ከምትገለጽባቸው እሴቶች መካከል ትብብር እና መተሳሰብ እንዱ መኾኑን ተናግረዋል። አሚኮ ከድጋፉም በላይ የትምህርትን አስፈላጊነት እና ካጋጠመው ችግር እንዲወጣ ሙሉ ጊዜውን እና አቅሙን አሟጦ እየሠራ መኾኑን በመጥቀስ ዶክተር ሙሉነሽ ኮርፖሬሽኑን አመሥግነዋል።
ዶክተር ሙሉነሽ በክልሉ ለትምህርት ዘመኑ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ደብተር፣ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን እስክርቢቶ፣ 50 ሺህ ዩኒፎርም እና 25 ሺህ የመርጃ መጻሕፍት ተሠብሥበው ለተማሪዎች እየደረሱ መኾኑን ገልጸዋል። ”ዛሬ አግዘን ያስተማርናቸው ልጆች ነገ ሀገር እንዲያግዙ የቤት ሥራ እየሰጠናቸው ነው” ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ከተረፈን ብቻ ሳይኾን ካለን ቀንሰን ትውልድን እንቅረጽ፤ የህሊና እርካታም እናግኝ ነው ያሉት።
ድጋፍ ያደረጉትን ሁሉ ያመሠገኑት ዶክተር ሙሉነሽ ሌሎችም በትውልድ ቀረጻ እና በመረዳዳት ዘመቻው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበሰላም እና በጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚመክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሄደ።
Next articleትምህርት አቋርጠው የከረሙ ተማሪዎች ለመማር መዘጋጀታቸውን ገለጹ።