የጋራ እንጅ የግል ባሕር የለም።

1
ባሕር ዳር: መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ታሪክ ተመራማሪ የኾኑት ሊንከን ፔይን“ ባሕር እና ሥልጣኔ፣ የዓለም የባሕር ታሪክ” በሚል ርእስ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 ባሳተሙት መጽሐፍ ዓለም አቀፍ ባሕርን ሀገራት በፍትሐዊነት እንዲጠቀሙበት ያትታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ1994 “የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ስምምነት” የተሰኘ ሕግን ደንግጎ ሥራ ላይ ማዋሉንም ገልጿል።
ሕጉም በ168 ሀገራት ጸድቆ ተግባራዊ ኾኗል።
ይህ “የባሕር ሕግ የጋራ እንጅ የግል ባሕር የለም” እንደሚል የጠቆሙት ተመራማሪው ሕጉን አብዛኞቹ የዓለም ሀገራት የተቀበሉት ታሪካዊ ስምምነት ነው።
በዚህ ሕግ አንቀጽ 69 ንዑስ አንቀጽ አንድ እስከ አምስት ድረስም የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ካለው ባሕር የተፈጥሮ ሃብት እኩል የመጠቀም መብትን አጎናጽፏቸዋል።
የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በተለየ ሁኔታ የባሕር በር ካለው ሀገር ጋር ወደውና ፈቅደው ስምምነት ካላደረጉ በስተቀር ለተገለገሉበት ባሕር (ወደብ) ምንም ዓይነት የትራፊክ ታክስ ወይንም ሌላ ክፍያ መክፈል እንደሌለባቸው ሕጉ በግልጽ አስፍሯል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም ዓቀፍ ባሕርን በጋራ መጠቀም የሚያስችል ሕግን በመደንገጉ እና ገቢራዊ በማድረጉም አብዛኞቹ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ እና ላቲን አሜሪካ ሀገራት የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአቅራቢያቸው ያለውን የባሕር በር (ወደብ) ተጠቃሚ አድርጓቸዋል።
በአፍሪካም ዛምቢያ እና ዚምባብዌ ወደብ አልባ ሀገራት ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት በደቡብ አፍሪካ የሚገኘውን የደርባን ወደብን እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
አውሮፓውይቷ ሀገር ጀርመን ኦስትሪያ፣ ስዊዘርላንድ እና ሉክሰምበርግን ጨምሮ ወደብ ከሌላቸው ሀገራት ጋር ድንበር ትጋራለች።
ጀርመን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የባሕር ሕግ ስምምነት መሠረት በማድረግም ወደብ የሌላቸው ጎረቤቶቿ ወደቦቿን እንዲጠቀሙ በማድረግ ጉርብትናዋን አጠናክራለች።
በደቡብ አሜሪካ የሚገኙት ፓራጓይ እና ቦሊቪያ ወደብ የሌላቸው ድንበር ተጋሪ ሀገራት ናቸው። ሁለቱ ሀገራት ከአርጀንቲና እና ብራዚል ጋር በመስማማት የሜርኮሱር የባሕር በርን በመጠቀም ላይ ናቸው።
እስያዊቷ ሀገረ ኔፓል ወደብ የሌላት ሀገር ናት፡፡ ከሕንድ ጋርም ድንበር ትጋራለች። ኔፓል እንደ ኮልካታ ያሉ የሕንድ ወደቦችን በመጠቀም የባሕር ላይ ንግድን ታከናውናለች፡፡
ሁለቱ ሀገራት ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በመተግበር ተጠቃሚ ኾነዋል፡፡ እንደ ኔፓል እና ሕንድ ወይም ዛምቢያ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች የባሕር ላይ መዳረሻ ወይም ወደብ ለሌላቸው ሀገራት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ወሳኝ ተሞክሮዎች ናቸው።
በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ መሠረትም ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ ሀገራት ሁሉ ድንበር በምትጋራው ቀይ ባሕር ላይ ከእነሙሉ ጥቅሙ የመገልገል መብት አላት።
ፕሮፌሰር አደም ካሚል ከሰሞኑ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የንግድ መስመር ነው። ለረጅም ዘመናትም ኢትዮጵያን ኃያል ሀገር እንድትኾን ያደረገ የታሪካችን መሠረት ነው ብለዋል።
ቀይ ባሕር ሀገራችን በታሪክ ያስመዘገበቻቸው የኃያልነት ሁነቶች ካስማም ነው ብለዋል። በጠቅላላው ባሕሩ መለያችን ኾኖ ሕዝባችን የቀይ ባሕር ንጉስ፤ ባሕሩም በቅጽል ስሙ “የሀበሻ ባሕር” የሚል ስያሜ እንደነበረው አስረድተዋል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየባሕር በርን ጉዳይ ከግብ ለማድረስ የውስጥ አንድነትን ማጠናከር ይገባል።