በምሥራቅ ጎጃም ዞን የተሰማሩ የልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢ እና የማኅበረሰብ ደኅንነትን ጠብቀው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው

4
ደብረ ማርቆስ: መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን አካባቢና ደን ጥበቃ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን እና ተግባር መሠረት የአካባቢ ብክለትን እና የብዝኀ ሕይወት መመናመንን በመከላከል፣ የአካባቢ፣ የደን እና የዱር እንስሳት ጥበቃ እና ልማት ሥርዓትን ለማስፈን እየሠራ ይገኛል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ በዞኑ ወደ ሥራ የገቡ የልማት ፕሮጀክቶች ልማትን ከአካባቢ ጥበቃ እና ማኅበረሰብ ደኅንነት ጋር ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል የቁጥጥር እና ክትትል ሥራ እየሠራ መኾኑን የተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ መለሰ መንግሥት ተናግረዋል።
በዞኑ ባለፈው በጀት ዓመት ከ550 በላይ የሚኾኑ የልማት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ በመሥራት የይሁንታ ሰርተፍኬት አረጋግጦ በመስጠት በሕጋዊ መንገድ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።
የአካባቢ ብክለት በማድረስ በማኅበረሰቡ አኗኗር ላይ ተፅዕኖ ያሳደሩ 40 የሚኾኑ ፕሮጀክቶች ላይም ቁጥጥር በማድረግ በገቡት ውል መሰረት የተፅዕኖ ማቅለያ ስልቶችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የማስተካከያ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቁመዋል።
በአንዳንድ በርሃማ አካባቢዎች በተፈጥሮ ደኖች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ እና ለመቆጣጠር የተደራሽነት ችግር መኖሩን ያነሱት ኀላፊው በችግር ውስጥ ኾኖም ባለፈው የ2017 ዓ.ም 36 ሺህ ሄክታር የተፈጥሮ ደን እንዲጠበቅ ጥረት መደረጉን አንስተዋል።
የደን ውጤቶች ዝውውር ሕጋዊ በኾነ መንገድ እንዲከናወን እና ከዘርፉ ተገቢውን ገቢ ለማግኘትም ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በጋራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያግዙ የኀይል አማራጮች ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እንዲኾኑ የማስተባበር ሥራ መሠራቱን አስገንዝበዋል።
ዘላቂ እና ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ሚናቸው የጎላ መኾኑን የጠቆሙት ኀላፊው ዞኑ ባለው የተፈጥሮ ፀጋ ልክ እንዲለማ ከባለድርሻዎች ጋር በትብብር እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የአካባቢ ብክለት እና ብክነትን ለመከላከል የሁሉን ትጋት ይጠይቃልም ብለዋል። በ2018 በጀት ዓመት የታለመውን ውጤት ሊያመጣ የሚችል ሥራ ለማከናወን ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየራስ የነበረን የባሕር በር አጥቶ ለችግር መጋለጥ ያስቆጫል።
Next articleየባሕር በርን ጉዳይ ከግብ ለማድረስ የውስጥ አንድነትን ማጠናከር ይገባል።