የራስ የነበረን የባሕር በር አጥቶ ለችግር መጋለጥ ያስቆጫል።

4
ደሴ: መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር በር አልባ መኾን ሀገር በድህነት ትማቅቅ ዘንድ ፈቅዶ እንደመቀበል መኾኑን የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የራስ የነበረን የባሕር በር አጥቶ ለችግር መጋለጥ ያስቆጫል ነው ያሉት ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ ነዋሪዎች።
ወደብ ለሀገር እድገት እና ሕልውና በጣም አስፈላጊ ነው። በባሕር በር እጦት ከተቸገሩ 17 የአፍሪካ እና 44 የዓለም ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት። እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚኾነውን የሀገራቸውን ጥቅል እድገት ያጣሉ።
ኢትዮጵያ ለዘመናት የባሕር በር ባለቤት ኾና የኖረች ሀገር ናት። ቀይ ባሕር ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተሳሰረ እና የማይነጣጠል ነው። ቀይ ባሕር ሲነሳ ባለቤቷ እና ታላቋ ኢትዮጵያ አብራ ትነሰላች። የኢትዮጵያ ታሪክም ሲነሳም ቀይ ባሕር ይነሳል።
ባለፉት ሦሥት አሥርት ዓመታት ግን በፖለቲካ ሸፍጦች ምክንያት ኢትዮጵያ ከባሕሯ ተገልላ ቆይታለች። ኢትዮጵያ በፖለቲካ አሻጥር ያጣችውን ባሕሯን ለማግኘት ጽኑ ጥያቄ አቅርባለች።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ የነበራቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎች የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ለዘርፈ ብዙ ችግር የተጋለጡ ናቸው ብለዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ዘሪሁን ማንደፍሮ ከ30 ዓመታት በፊት የተሠራው ስህተት የራሳችን የኾነውን የባሕር በር አጥተን ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ ችግሮች ዳርጎናል ብለዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር በማጣቷ ቁጭት እንደፈጠረባቸውም ተናግረዋል።
በርካታ የሕዝብ ቁጥር ባለው ሀገር ውስጥ የባሕር በር ከንግድ ማሳለጫነት በላይ የሕልውና ጉዳይ ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ዘቢብ ዳውድ ናቸው።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አሕመድ የሱፍ የሀገራችን ተፈጥሯዊ ወሰኗ ቀይ ባሕር እስትንፋሷ፣ የባሕል፣ የታሪክ እና የሕይወት ማሰሪያ ውሏ ነው ብለዋል። ሀገራችንም በሰጥቶ መቀበል መርህ የባሕር በር ባለቤት የምትኾንበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ጽኑ እምነት እንዳላቸው ነው የተናገሩት።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ሉባባ ሁሴን የባሕር በር ባለቤት መኾን የሀገርን እድገት እና ዘላቂ ሰላምን የሚያስገኝ፣ የዜጎችን የወደፊት ተስፋ የሚያለመልም ዋነኛ መንገድ ነው ብለዋል።
መንግሥት ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትኾን በተለያየ መልኩ እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ አንተነህ ጸጋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የኢትዮጵያውያን የጋራ አቋም ሊኾን ግድ ይላል።
Next articleበምሥራቅ ጎጃም ዞን የተሰማሩ የልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢ እና የማኅበረሰብ ደኅንነትን ጠብቀው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው