የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የኢትዮጵያውያን የጋራ አቋም ሊኾን ግድ ይላል።

3
ደሴ፡ መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የልማት ጉዟቸውን ስኬታማ ለማድረግ የባሕር በር ያስፈልጋቸዋል።
የኢኮኖሚ ማደግ እና የመልማት ፍላጎትን ተከትሎ የባሕር በር አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም የሚሉት በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንድሪስ ሁሴን የባሕር በር ለኢትዮጵያውያን የሕልውና ጉዳይ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በታሪክ ስህተት ኢትዮጵያ የባሕር በር ብታጣም ያሉትን አማራጮች በመጠቀም እንደቀደመው ጊዜ የባሕር በር ባለቤት መኾን ይገባታል ነው ያሉት። ለዚህም ሰላማዊ መንገድን መከተል ቀዳሚ ምርጫ መኾኑን ተናግረዋል።
እንደ መምህሩ ገለጻ አንድነት ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ ነው። አንድነትን በማጠናከር በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለባሕር በር ጥያቄ እና ፍላጎት መሳካት መተባበር ይገባቸዋልም ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ እና በጠነከረ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ መሳካቱን ያነሱት መምህሩ የባሕር በርን ጨምሮ ሌሎች ብሔራዊ ጥቅሞችን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን አንድ በመኾን ማሳካት አስፈላጊ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ የባሕር በር ጠቃሚነትን በትውልዱ ውስጥ ማስረጽ ይገባል ነው ያሉት።
የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ለበርካታ ፈተናዎች የተጋለጡ መኾናቸውንም አንስተዋል። በዋናነት ውቅያኖስ ጋር መድረስ ስለማይችሉ የሸቀጦችን ምልልስ ውድ እና ጊዜ የሚወስድ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። በዓለም አቀፍ ንግድ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጠቁመዋል።
እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የባሕር በር ሲዘጋባቸው ለትራንስፖርት እና ለማሪታይም ንግድ በጎረቤት ሀገራት ላይ ጥገኛ ለመኾን ይገደዳሉ ነው ያሉት።
የባሕር በር አልባነት ለከፍተኛ የሸቀጦች ማመላለሻ ወጭ በማጋለጥ ሀገሪቱን ለኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች እያጋለጣት መኾኑን አመላክተዋል።
የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እና በዓለም አቀፍ ንግድ ለመሳተፍ ይቸገራሉ ያሉት መምህሩ “የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ በመኾኑ የኢትዮጵያውያን የጋራ አቋም ሊኾን የግድ ይላል” ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሕይወት አስማማው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleምክር ቤቶች የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዋነኛ ዓላማቸው ነው።
Next articleየራስ የነበረን የባሕር በር አጥቶ ለችግር መጋለጥ ያስቆጫል።