
ባሕር ዳር: መስከረም 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ድጋፍ ለዞን፣ ለወረዳ እና ለከተማ ምክር ቤት ፎረሞች ሥልጠና እየሰጠ ነው።
የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ምክር ቤቶች የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዋነኛ ዓላማቸው ነው ብለዋል።
ሥልጠና በራሱ ግብ እና ስኬት አይደለም ያሉት አፈጉባዔዋ ክፍተትን እየሞሉ አጥጋቢ ሥራ ለመሥራት አጋዥ እንደኾነም ጠቁመዋል።
ከሥልጠናው በኋላም የሕዝብ ተወካይ የኾኑት የምክር ቤት አባላት የተሠሩ ሥራዎችን ለኀብረተሰቡ ማሳወቅ እና ለላቀ ሥራ መነሳሳት አለባቸው ብለዋል።
የአዊ ብሔረሰብ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሙሉአዳም እጅጉ የምክር ቤት አባላት ሥራዎችን ለመከታተል እና ለመቆጣጠር፣ ሕግ ለማውጣት እና የሕዝብ ውክልናን በአግባቡ ለመፈጸም ሥልጠናው ከፍተኛ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት።
የቀበሌ ምክር ቤቶች በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ኀላፊነት በአግባቡ እየተወጡ አይደለም ያሉት ወይዘሮ ሙሉአዳም አሁን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም በሕዝብ የተሰጠን ውክልና ገቢራዊ ለማድረግ የሥልጠናው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በሕግ መንግሥቱ የቀበሌ ምክር ቤቶች በአንድ ዓመት ውስጥ 12 ጊዜ ተከታታይ ጉባኤዎች እንዲደረጉ ይደነግጋል ነው ያሉት። እስካሁን ያጋጠመውን ክፍተት ለመሙላት ሥልጠናው ስንቅ ይኾናል ነው ያሉት።
ከሥልጠናው ተመልሰው ምክር ቤቶች ተከታታይ ሥልጠናዎችን በማከናዎን ሞዴል ቀበሌዎችን እና ወረዳዎችን ለመፍጠር ይሠራሉ ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጌትነት ዕውነቱ (ዶ.ር) የሕዝብ ተወካይ የኾኑት ምክር ቤቶች ሥራቸውን ማከናወን ያለባቸው በዕውቀት ላይ ተመርኩዘው መኾን ይገባቸዋል ብለዋል።
ሕዝቡ ምንድን ነው የሚፈልገው የሚለውን የሚረዳ ሞጋች የምክር ቤት አባላት ያስፈልጋል ያሉት አፈጉባኤው ለዚህ ደግሞ የአቅም ግንባታ ሥልጠናው ችግሮች እንዳይፈጠሩ እና ከተፈጠሩ በኋላም ችግሮችን ለመፍታት ያግዛል ነው ያሉት።
ሥልጠናውን በተዋረዱ ለሚገኙ አባላትም እንዲሰጥ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ዝግጁ እንደኾኑም ገልጸዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን የጃቢህ ጠናን ወረዳ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ዓባይነህ ፀሐይ እንዳሉት ክልሉ የጸጥታ ችግር ውስጥ በመኾኑ ምክር ቤቶች ተቀዛቅዘው ቆይተዋል። ሥልጠናው ከነበረው ቁዘማ የሚመልስ እና ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!