ምክር ቤቶች ሕዝብ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲኾን መሥራት ይገባቸዋል።

4
ጎንደር: መስከረም 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ለዞን፣ ለወረዳ እና ለከተማ ምክር ቤት ፎረሞች የተዘጋጀ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በጎንደር ከተማ እየሰጠ ነው።
ምክር ቤቱ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ የሚገኘው።
በሥልጠናው ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ምዕራብ ጎንደር ዞን፣ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አፈ ጉባኤዎች እና ቋሚ ኮሚቴዎች ተሳታፊ ኾነዋል።
ሥልጠናው የምክር ቤቶች ኀላፊነት እና የሥራ ድርሻ ላይ ትኩረት ያደረገ መኾኑም በውይይቱ ተነስቷል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ልዩ አማካሪ ደብረወርቅ ይግዛው ሥልጠናው የምክር ቤቶች ተልዕኮ ላይ ግልጽነት መፍጠር፣ ውጤታማ የምክር ቤት አፈጻጸም እንዲኖር መሥራት፣ የልምድ ልውውጥ ማድረግ እና ትክክለኛ አሠራሮችን ማሳወቅን ያለመ መኾኑንም ገልጸዋል።
ምክር ቤቶች ሕዝብ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲኾን መሥራት ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ለአፈ ጉባኤዎች እና ለምክር ቤት አባላት የሚሰጠው ሥልጠና ምክር ቤቶች የአሥፈፃሚዎችን ተግባራት በአግባቡ ተረድተው ለመከታተል እና ኀላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት የሕዝቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ ያስችላል ብለዋል።
የምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ውዴ የሽመብራት ሥልጠናው የሚከናወኑ ተግባራትን ይበልጥ ለማወቅ ዕድል የፈጠረ መኾኑን ገልጸዋል።
የተሰጠውን ሥልጠና ወደ ተግባር በመቀየር በተያዘው በጀት ዓመት የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካት እንደሚሠሩም አመላክተዋል።
የነባሩ ጭልጋ ወረዳ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በለው አዘዘው “ግንዛቤን የሚፈጥር ሥልጠና ነው” ብለዋል። የዕድገት እና የልማት ተግባራትን ለመደገፍ የሚያስችል ሥልጠና መውሰዳቸውንም ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጭዎቹ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ለሕዝብ ተጠቃሚነት እንደሚሠሩም አንስተዋል። ሥልጠናው ለሌሎች የምክር ቤት አባላት ተደራሽ እንደሚኾንም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክር ቤቶች የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከእስካሁኑ የበለጠ መሥራት አለባቸው፡፡
Next articleየሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለሚያመርቱ ድርጅቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል።